ቀጥታ፡

በአቪዬሽን ዘርፉ የሚታየውን የግንዛቤ ክፍተት ለመሙላት ያግዛል የተባለ መፅሃፍ ለንባብ በቃ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 17/2013( ኢዜአ) በአቪዬሽን ዘርፉ የሚታየውን የግንዛቤ ክፍተት ሊሞላ ይችላል የተባለው "አውሮፕላን እንዴት ይበራል" በሚል ርእስ የተዘጋጀው መፅሃፍ ለንባብ በቃ።

በመጽሐፉ ምረቃ ላይ  ሃያሲና ደራሲ ደረጄ በላይነህ፣ የመገናኛ ብዙሃን አማካሪ አቶ ውሁድ ቤናሚን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን አብራሪዎች ማህበር ካፒቴኖችና ሌሎች ሰራተኞች ታድመውበታል።

የመፅሃፉ ደራሲ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ሲኒየር ቴክኒሻን አብርሃም ደበሌ፤ እስካሁን በአውሮፕላን በረራና በዘርፉ ያሉ ሌሎች ግንዛቤዎች ዙሪያ በአገር ውስጥ ቋንቋ የተፃፉ አጋዥ መፃህፍቶች አለመኖራቸውን ገልጸዋል።

በመሆኑም ''አውሮፕላን እንዴት ይበራል'' በሚል የተፃፈውና ዛሬ የተመረቀው መጽሐፍ በአቪዬሽን ዘርፉ የሚታየውን የግንዛቤ ክፍተት ለመሙላት ይረዳል በሚል እንዳዘጋጁት ገልጸዋል።

መጽሐፉ የአውሮፕላን የበረራ ሚስጥር፣ አውሮፕላንን ለመፍጠር እነማን ሞከሩና ተሳካላቸው፣ ለመብረር አስተዋጽኦ የሚያደርጉ የአውሮፕላን አካላት፣ አውሮፕላን ለማምረትና ለማብረር የሚሳተፉ ባለሙያዎች እነማን ናቸው የሚሉ ጉዳዮች ላይ ያተኩራል።

በዘርፉ ከንድፈ ሀሳብ ጀምሮ እስከ ማምረት የሚኖረውን ጉዞ ለማስቃኝት  በመጽሐፉ ሙያዊ ቃላቶችን ቀለል ባለ አማርኛ ለመመለስ ጥረት መደረጉንም አብራርተው፤በቀጣይ ''ወደ አቪዬሽን ኢንዱስትሪው መቀላቀል የሚፈልጉ ሰዎች በሙሉ፤ እኔ ያጋጠመኝን ችግር ሳይጋፈጡ በቀላሉ ግንዛቤ ያገኙበታል'' ብለዋል፡፡

ሌሎች በዘርፉ የተሻለ እውቀትና ክህሎት ያላቸው ባለሙያዎችም በተመሳሳይ እውቀታቸውን ለሌሎች እንዲያካፍሉ መነሳሳትን ይፈጥራል የሚል እምነት አለኝም ብለዋል።

አሁን በአማርኛ ለህትመት የበቃውን መፅሃፍ በቀጣይ በትግርኛና በኦሮምኛ ቋንቋዎች ተተርጉሞ ለንባብ እንደሚበቃ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ አብራሪዎች ማህበር ተወካይ ካፒቴን አዲስ ወልደሚካኤል፤ በሀገሪቱ በተለይ በአቪዬሽን መስኩ ሙያዊ የሆኑ መጽሀፍቶች በአማርኛ ቋንቋ እንዳልተፃፉ አንስተዋል።

በመሆኑም ለመጀመሪያ ጊዜ በአማርኛ ቋንቋ የተፃፈው ይሄው መፅሐፍ ለኢንዱስትሪው እድገት ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው በማመን ማሕበሩ የሕትመቱን ሙሉ ወጪ መሸፈኑን ገልፀዋል።

በምርቃቱ ላይ የተገኙት ካፒቴን የሽዋስ ፋንታሁን በበኩላቸው "ከዚህ በኋላ በርካታ ኢትዮጵያዊያን መረጃ አግኝተው ወደ አቬዬሽን ኢንዱስትሪው  እንደሚቀላቀሉ እርግጠና ነኝ" ብለዋል፡፡

ሃያሢና ደራሲ ደረጄ በላይነህ፤ ፀሐፊው ፈርቀዳጅ በመሆናቸው ሌሎችንም እንደሚያበረታታ ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም