በደቡብ ኦሞ ዞን የሚፈጸሙት ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች ከተለመዱት የተለዩና እጅግ ጎጂ መሆናቸውን ጥናት አመለከተ

146

ታህሳስ 17 ቀን 2013 (ኢዜአ) በደቡብ ኦሞ ዞን የሚፈጸሙት ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች ከተለመዱት የተለዩና እጅግ ጎጂ መሆናቸውን ጥናት አመለከተ።

በደቡብ ኦሞ ዞን ያሉትን የጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ለመከላከል የሀይለማሪያምና ሮማን ፋውንዴሽን ከፊንላንድ ኤምባሲ በተገኘ ድጋፍ ጥናት ተካሂዷል።

በጥናቱ እንደተመላከተው በአካባቢው እየተፈጸመ ያለው ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች የተለዩና እጅግ ጎጂዎች ናቸው።

ከንፈር መተልተል፣ ከቤት ውጪ መውለድ፣ ሴትን ልጅ በህይወት ለሌለ ሰው መዳር፣ የሴት ልጅ ግርፋት፣ ህጻናትን ‘ገፊ’ ብሎ መጣል፣ ከፍተኛ ጥሎሽ መጠየቅና መቀበል፣ እንዲሁም ሴት ትዳር ከያዘች በኋላ መብት ሳይኖራት ባርነት በመሰለ ሁኔታ እንድትኖር ማድረግ በአካቢው ከሚፈጸሙት ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ውስጥ እንደሚገኙበት ጥናቱ ጠቅሷል።

ድርጊቶቹ በማህበረሰቡ ውስጥ እየተፈጸሙ የሚገኙት ግንዛቤ ከማጣት እንደሆነም ተጠቁሟል።

ችግሩን ለመፍታትና ድርጊቶቹ በማህበረሰቡ ላይ የሚያሳድረውን ጫና ለመቀነስ መስራት እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።

በተለይም ሴቶች ያሉባቸውን ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መፍታት፣ ተቀናጅቶ መስራት፣ የግንዛቤ ፈጠራ ስራ ማከናወንና ለሴቶች የዓቅም ግንባታ ስልጠና መስጠት የችግሩን መጠን ለመቀነስ እንደሚያስችል ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም