ቀጥታ፡

የቀድሞ የደርግ ባለስልጣናት በአመክሮ እንዲለቀቁ መደረጉ የሰብአዊ መብት መርህን የተከተለ እርምጃ ነው - ዶክተር ዳንኤል በቀለ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 17/2013 ( ኢዜአ) የቀድሞ የደርግ ባለስልጣናት በአመክሮ እንዲለቀቁ መደረጉ የሰብአዊ መብት መርህ የተከተለ ጠቃሚ እርምጃ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ ገለጹ።

ኮሚሽኑ ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት ስራውን በነጻነት እያከናወነ ነውም ብለዋል።

አዲስ አበባ በሚገኘው የጣልያን ኤምባሲ ለ30 ዓመት ተጠልለው የነበሩት የቀድሞ የደርግ ባለስልጣናት ሌተናል ኮሎኔል ብርሃኑ ባየህና ሌተናል ጄኔራል አዲስ ተድላ በአመክሮ እንዲለቀቁ መደረጉን የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የሙስና እና የተደራጁ ወንጀል ጉዳዮች ዘርፍ ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አቶ ፍቃዱ ጸጋ ከትናንት በስቲያ መግለጻቸውን ይታወሳል።

የተለቀቁበትም ሂደት የወንጀል ሕጉንና ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን የተከተለ መሆኑን ተናግረዋል።

ባለስልጣናቱ የፍርድ ሂደታቸው በሌሉበት የታየና የጥፋተኝነት ውሳኔ ተላልፎባቸው የሞት ፍርድ የተወሰነባቸው ነበሩ።

የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የሁለቱን ባለስልጣናት የሞት ቅጣት ወደ እድሜ ልክ እስራት እንዲቀየርላቸው በፊርማቸው ማጽደቃቸውም ይታወሳል።

ከግንቦት 1983 ዓ.ም ጀምሮ በጣልያን ኤምባሲ ተጠልለው የነበሩት ባለስልጣናት በኤምባሲው የቆዩበት ጊዜና የጤና ሁኔታቸውን ታሳቢ በማድረግ በአመክሮ ተለቀው ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲቀላቀሉ ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል  ከዚህ በፊት በፍርድ ቤት የቀድሞ የደርግ ባለስልጣናት በአመክሮ ይለቀቁ እንደነበር አውስተዋል።

በዚሁ መንፈስ ሁለቱ ባለስልጣናት በአመክሮ እንዲለቀቁ መደረጉ ከሰብአዊ መብት መርህ አንጻር ጠቃሚ የሆነ እርምጃ መሆኑን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ግጭትን ተከትሎ የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች እየተባባሱ መምጣታቸውን ዋና ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

መንግስት ለሚከሰቱት ግጭቶች የሚሰጠው ፖለቲካዊ መፍትሔ እንዳለ ሆኖ የሰብአዊ መብት ጥሰት የሚፈጽሙትን አካላት ለፍርድ ማቅረብና ተጎጂዎችን ለመካስ መስራት ይገባዋል ብለዋል።

ኮሚሽኑ ያለ ምንም ጣልቃ ገብነት ስራውን በነጻነት እየሰራ መሆኑን የተናገሩት ዶክተር ዳንኤል፤ ኮሚሽኑ የማንንም ጣልቃ ገብነት እንደማይቀበልም ተናግረዋል።

ኮሚሽኑን ጨምሮ የዴሞክራሲ ተቋማት ነጻና ገለልተኛ የሚያደርጉ የለውጥ እርምጃዎች መልካም የሚባሉና ሊጎለብቱ እንደሚገባቸውም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም