ጤናማ የሥራ አካባቢን ለማመቻቸት እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ጤናማ የሥራ አካባቢን ለማመቻቸት እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ገለጸ
ጎባ፣ ታህሳስ 17/2013 (ኢዜአ) ሠራተኞቹን ከኤች አይ ቪ ኤድስና ኮሮና ቫይረስ በመጠበቅ ጤናማ የሥራ አካባቢን ለማመቻቸት በትኩረት እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ገለጸ።
የአገልግሎቱ ባሌ ሮቤ ዲስትሪክት ሠራተኞች የፀረ ኤች አይቪ ኤድስ ቀንን በፓናል ውይይትና ደም ምርመራ በማካሄድ አክብረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አህመድ በዳሶ እንዳሉት መስሪያ ቤቱ ሠራተኞቹን ከኤች አይ ቪ ኤድስና ኮሮና ቫይረስ ለመጠበቅ ስትራቴጂክ ዕቅድ ነድፏል፡፡
በዚህም ተጋላጭነት በመከላከል ጤናማ የሥራ አካባቢን ለማመቻቸት እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በኤሌክትሪክ አገልግሎቱ ደረጃ በየዓመቱ የሚከበረው የፀረ ኤች አይ ቪ ቀን ምክንያት በማድረግ ሠራተኞች ራሳቸውን አውቀው እንዲጠነቀቁ ለማስቻል የደም ምርመራ ማካሄዳቸው የመከላከሉ ሥራ አንዱ አካል እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
ምረመራ በማድረግ ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝባቸው ሠራተኞች የሚደገፉበት ሁኔታ እየተመቻቸ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በአገልግሎቱ የባሌ ሮቤ ዲስትሪክት ኃላፊ አቶ ማህሙድ ሁሴን ናቸው፡፡
በኤሌክትሪክ አገልግሎቱ ደረጃ ቀኑ ሲከበር በዓመቱ ኤች አይ ቪ/ኤድስን ለመከላከል በተከናወኑ ስራዎች ዙሪያ በመወያየት ቀጣይ አቅጣጫዎች እንደሚመላከቱ ገልጸዋል፡፡
የአገልግሎቱ ሠራተኛ የሆኑት አቶ አየለ ሀይለጊዮርጊስ በሰጡት አስተያየት ቫይረሱ በደማቸው እንዳለ ከአስር ዓመታት በፊት እንዳወቁ ተናግረዋል።
በጤና ባለሙያ የሚሰጣቸውን ምክር በአግባቡ ተግባራዊ በማድረጋቸው በጥሩ ጤንነት ላይ እንደሚገኙም ተናግረዋል፡፡
አቶ አየለ በአሁኑ ወቅት ከቫይረሱ ጋር ተያይዞ በህብረተሰቡ ዘንድ የሚስተዋለው መዘናጋት ዋጋ እንዳያስከፍል ጥንቃቄ እንዲያደርግ መክረዋል።
ራሳቸውን ለማወቅ በበዓሉ አከባበር ወቅት የደም ምርመራ ካደረጉ የአገልግሎቱ ሠራተኞች መካከል አቶ ግሩም ውቤ በበኩላቸው የደም ምርመራ በማድረጌ እራሴን በማወቅ ቤተሰቤንና ማህበረሰቡን ለመጠበቅ ይረዳኛል ብለዋል፡፡
መመርመሯ እራሷን በማወቅ ጤንነቷን እየጠበቀች ለማህበረሰቡ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያግዛት የተናገረችው ደግሞ ሌላው የአገልግሎቱ ሠራተኛ ወጣት ገነት ኡመር ናት፡፡
ሌሎች ሠራተኞችም ተመርምረው ውጤታቸውን ቢያውቁ ደህንነቱ የተጠበቀ ጥሩ አገልግሎት ለህብረተሰቡ መስጠት እንደሚያስችላቸው አስተያየቷን ሰጥታለች።