ቀጥታ፡

ረቂቅ ዓዋጁ ዓለም አቀፍ ሁኔታን ያገናዘበና የውጭ ግንኙነትን የሚያሳልጥ ነው

አዲስ አበባ ታህሳስ 16/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ ረቂቅ ዓዋጅ ዓለም አቀፍ ሁኔታን ያገናዘበና ግንኙነትን እንደሚያሳልጥ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ገለጹ። 

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ጋር በመሆን ዛሬ ከባለድርሻ አካላትጋር የምክክር መድረክ አካሂዷል።

ረቂቅ ዓዋጁ "የኢትዮጵያ ንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ" ተብሎ ቀርቧል።

የምክር ቤቱ ዋና ፀሐፊ አቶ ጌታቸው ረጋሳ ለኢትዮጵያ የንግድ ማህበረሰብ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግስት ጀምሮ ሶስት ማቋቋሚያ ዓዋጆች እንደተዘጋጁላቸው ያስታውሳሉ።

የኢህአዴግ መንግስት የስርዓቱ ባለሃብቶችን ለመፍጠር በሚያደርገው እንቅስቃሴ ገበያውንም ሆነ የንግድ እንቅስቃሴ በመቆጣጠር ንግድ ምክር ቤቶችን ልይስሙላ አደራጅቷል ብለዋል።   

ለዚህ መሳሪያ ሆነው ካገለገሉ እርምጃዎች መካከልም ላለፉት 18 ዓመታት ሲያገለግል የነበረው አዋጅ ቁጥር 341/1995 መሆኑን ጠቁመዋል።

አዋጁ ንግድና ዘርፉ ተስማምቶ እንዳይሰራ ያደረገ፣ ምክር ቤቶችን ከማጠናከር ይልቅ ፖለቲካዊ ጠቀሜታ እንዲኖረው ታስቦ የወጣ በመሆኑ ውስብስብ ችግሮችን ፈጥሯል ብለዋል።

በአንጻሩ አሁን የቀረበው ረቂቅ ዓዋጅ ነፃ፣ ትክክለኛ፣ ጠንካራና በእውቀት ላይ የተመሰረተ የሕግ ማዕቀፍና የተደራጀ የንግድና ኢንቨስትመንት ስርዓት የሚዘረጉ ምክር ቤቶችን ማደራጀት የወቅቱ ጥያቄ ነው ብለዋል።

ረቂቅ ዓዋጁ ባለሃብቱ በእኩልነት፣ በብቃትና በጥንካሬ አገልግሎት የሚያገኝባቸው ተቋማት ለመፍጠር ትኩረት እንዲሰጥ አቶ ጌታቸው ጠይቀዋል።  

የሕግ ማዕቀፎች ዓላማቸውን ቁጥጥር ከማድረግ ተላቀው የግሉ ዘርፍ በነፃነት የሚንሸራሸርበት የንግድና ኢንቨስትመንት ምህዳር መፍጠር እንደሚገባ አመልክተዋል።

ለግሉ ዘርፍ መብት መከበር የሚሰራ፣ ነፃ ውድድር ያለበት እንዲሁም የንግድና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴን የሚያጎለብት ተቋም እንደሚያስፈልግም ዋና ፀሐፊው ተናግረዋል።

የነጋዴው ማኅበረሰብ በአገሪቷ እድገት ያለውን ተሳትፎ ለማሳደግ ቀድሞ የነበረው አሰራር መሻሻል አለበት ያሉት ደግሞ የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መሰንበት ሸንቁጤ ናቸው።

ረቂቅ ዓዋጁ የንግዱ ማኅበረሰብ አገር አቀፍ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ ሁኔታን ያገናዘበና ከዓለምአቀፍ ተቋማት ጋር ያለውን ግንኙነት ለማሳለጥ ያስችላል ብለዋል።

አገሪቷ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠናን ለመቀላቀልና የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን እየተዘጋጀች ከመሆኗ አኳያም ጠቀሜታው የላቀ መሆኑን ፕሬዚዳንቷ አስታውቀዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎችም የንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ ዓዋጆች ዘመን ተሻጋሪ ሆነው መዘጋጀት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

የምክር ቤቱ አወቃቀር ወቅቱ በሚጠይቀው መልኩ ሊሆን ይገባዋል ነው ያሉት።     

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ እሸቴ አስፋው ሚኒስቴሩ ከአውሮፓና ከአፍሪካ አገራት ልምዶች በመውሰድ ረቂቅ ዓዋጁን ማዘጋጀቱን ተናግረዋል።

ከተሳታፊዎች የሚሰበሰቡ ሃሳቦችን ረቂቅ ዓዋጁን የተሟላ ለማድረግና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ለማዳበር እንጠቀምበታለን ብለዋል።

ሚኒስቴሩ የንግድ ስርዓቱን በማዘመንና ምርታማነትን ለማሳደግ እያደረገ ያለውን ክትትልና ድጋፍ እንደሚያጠናክርም አቶ እሸቴ  አስታውቀዋል።  

የምክክር መድረኩ ረቂቅ ዓዋጁ ፀድቆ ወደ ስራ ከመግባቱ በፊት የጉዳዩን ባለቤቶች ገንቢ ሃሳቦች ለማሰባሰብ መዘጋጀቱን ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም