ሁለተኛው ዙር ተሳትፏዊ አነስተኛ መስኖ ልማት ፕሮግራም በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሁለተኛው ዙር ተሳትፏዊ አነስተኛ መስኖ ልማት ፕሮግራም በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች እየተካሄደ ነው
አዳማ ሀምሌ 14/2010 በአገሪቱ ከ145 ሚሊዮን ዶላር በሚበልጥ ወጪ ሁለተኛው ዙር ተሳትፏዊ አነስተኛ መስኖ ልማት ፕሮግራም እየተካሄደ መሆኑን የግብርናና እንስሳት ሃብት ሚኒስቴር አስታወቀ። በሚኒስቴሩ አዘጋጅነት " የተሳትፏዊ አነስተኛ መስኖ ልማት ፕሮግራም የግብዓትና የምርት ግብይት ፎረም " ዛሬ በዝዋይ ባቱ ከተማ ተጀምሯል። የፕሮግራሙ ብሔራዊ አስተባባሪ አቶ ኑረዲን አሳሮ ለኢዜአ እንደገለጹት ፕሮግራሙ ከ2009 ዓ.ም ታህሳስ ወር ወዲህ እየተካሄደ ያለው በትግራይ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች በተመረጡ 110 ወረዳዎች ውስጥ ነው። ለስድስት ዓመታት ተግባራዊ በሚሆነው በእዚህ ፕሮግራም ከ150 በላይ አነስተኛ መስኖ ፕሮጀክቶች በወረዳዎቹ እንደሚገነቡ አስታውቀዋል። በዚህም ከ18 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ በማልማት የምግብ ዋስትና ችግር ያለባቸውን ከ600 ሺህ በላይ አርሶና ከፊል አርብቶ አደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ ግብ መያዙን ነው ያስታወቁት። እስካሁን በተደረገ እንቅስቃሴም ዝርዝር ጥናትና ዲዛይን ተሰርቶላቸው ግንባታቸው ከተጀመረው ከ50 በላይ የመስኖ ፕሮጀክቶች መካከል 20ዎቹ ተጠናቀዋል። በተጠናቀቁት የመስኖ እውታሮችም 3 ሺህ 500 ሄክታር መሬት ላይ በፕሮግራሙ የታቀፉ 18 ሺህ አባውራዎች በገበያ ተፈላጊ የሆኑና የተመረጡ ምርቶችን እንዲያለሙ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል። አቶ ኑረዲን እንዳሉት ወንዞችን በመጥለፍ፣ የከርሰ ምድር ውሃን በመቆፈርና ለቆላማ አካባቢዎች ከደጋና ወይናደጋ አካባቢ የሚጥለውን ዝናብ ተከትሎ የሚመጣውን ጎርፍ በመያዝ ለመስኖ ልማቱ ለማዋል እየተሰራ ነው። በተለይ በፕሮግራሙ ቀጥታ ተጠቃሚ ለሆኑ ከ46 ሺህ በላይ አባወራዎች የመስኖ ኤክስቴንሽን አገልግሎት ስልጠና የመስጠት፣ የተለያዩ የምርት ማሳደጊያ ግብዓቶችና ቴክኖሎጂዎች በዘላቂነት የሚያገኙበትን ሁኔታ የማመቻቸትና በግብይት የማስተሳሰር ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል። ፕሮግራሙ በዓለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድና በኢትዮጵያ መንግስት የፋይናንስ ድጋፍ የሚካሄድ ሲሆን ዋና ዓላማውም የገጠሩን ሕብረተሰብ ኑሮ ማሻሻል፣ የገቢ ምንጭ ማሳደግና የምግብ ዋስትናቸውን በዘላቂነት ማረጋገጥ መሆኑን አቶ ኑረዲን ገልጸዋል። በመድረኩ ላይ የተገኙት የፌዴራል ኀብረት ሥራ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲ ሙመድ በበኩላቸው ፕሮግራሙ ገጠርን ማዕከል ያደረገ ዘላቂነት ያለው የኢኮኖሚ ልማትን ዕውን ለማድረግ አስተዋጽኦው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል። በመንግስትና በልማት አጋሮች ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የሚገነቡ የመስኖ ተቋማት ዘመናዊ የእርሻ ዘዴን ለማስፋፋት፣ በቂና ጥራት ያለው ምርት ለማምረትና በወቅቱ ለገበያ በማቅረብ አርሶ አደሩና ኀብረት ሥራ ማህበራት ከዘርፉ የተሻለ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደርጋል" ብለዋል። እንደአቶ አብዲ ገለጻ ከፕሮግራሙ የትኩረት መስኮች መካከል ከ68 ሺህ ሄክታር በላይ የተፋሰስ ልማትን ማካተቱ በዘላቂነት ልማትን ለማረጋገጥ ያስችላል። ፕሮግራሙ ከሚካሄድባቸው አካባቢዎች መካከል በአማራ ክልል አዊ ብሔረሰብ ዞን የሚገኘው የዘንገና የመስኖ ግብዓት አቅርቦትና ምርት ግብይት ዩኒዬን አንዱ ነው። የዩኒየኑ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሐብታሙ አበራ በሰጡት አስተያየት እንዳሉት በፕሮግራሙ የዩኒዬኑ አባል ለሆኑ 10 የኀብረት ሥራ ማህበራት አባላት ስልጠና በመስጠት፣ የቢሮ ቁሳቁስ በማበርከትና በግብይት አሰራር ላይ ድጋፍ ተደርጓል። ዩኒየኑ ከጎንደር ብቅል ፋብሪካ፣ ከእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ፣ ከአዲስ አበባና ባህር ዳር የአትክልትና ፍራፍሬ ተጠቃሚዎች ጋር ያለውን የገበያ ትስስር በማጠናከር በ2011 በጀት ዓመት 240 ሺህ ብር የተጣራ ትርፍ ለማግኘት ማቀዱንም አስታውቀዋል። የተሳትፏዊ አነስተኛ መስኖ ልማት ፕሮግራም ከፍተኛ ባለሙያ ወይዘሮ ንግስት ከበደ በበኩላቸው "የጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት እንዲስፋፋና በተለይም ሴት አርሶ አደሮች በግልም ሆነ በቡድን ተጠቃሚ እንዲሆኑ ፕሮግራሙ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል" ብለዋል። ወይዘሮ ንግስት እንዳሉት በዋነኛነት ተጠቃሚ አባወራዎች፣ እማወራዎችና የልማት ሠራተኞችን አቅም ለማሳደግ የስልጠና ድጋፍ ይደረጋል። ለሥራው የሚያስፈልጉ ማቴሪያሎችና የትራንስፖርት መገልገያዎችም በፕሮግራሙ እንዲሟሉ ይደረጋል። መድረኩ አራቱ ክልሎች እርስ በርስ ልምድ እንዲለዋወጡና በ2011 ዓ.ም ፕሮግራሙን አስፋፍቶ መስራት በሚቻልበት መንገድ ላይ እንዲወያዩ ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑንም ገልጸዋል። ለአራት ቀን በሚቆየው በእዚህ መድረክ ላይ ፕሮግራሙ ከሚካሄድባቸው ክልሎች የተውጣጡ አስፈጻሚ አካላትና ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡