መከላከያ የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ መሪነቱን አጠናክሯል

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 16 /2013 (ኢዜአ) መከላከያ የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ መሪነቱን ያጠናከረበትን ድል አስመዘገበ። 

በፕሪሚየር ሊጉ የሦስተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም በሚገኘው እጅ ኳስ ሜዳ ተካሄደዋል።

መከላከያ ከጎንደር ከተማ ባደረጉት ጨዋታ መከላከያ 33 ለ 20 በሆነ ውጤት ተጋጣሚውን ያሸነፈ ሲሆን

በዚህም ነጥቡን ወደ ስድስት ከፍ በማድረግ የፕሪሚየር ሊግ መሪነቱን ማጠናከር ችሏል።

መከላከያ በመጀመሪያ ሁለት የሊጉ ጨዋታዎች አዲሱን የፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ ባህር ዳር ከተማና ፌዴራል ፖሊስን ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ በ2009 ዓ.ም ሲጀመር መከላከያ የሊጉ ውድድር የመጀመሪያ አሸናፊ መሆኑ አይዘነጋም።

በሌላ ጨዋታ የካቻምናው የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ሚዛን አማን ከተማን 36 ለ 22 አሸንፏል፤ ነጥቡንም ወደ አራት ከፍ በማድረግም ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

በአንጻሩ ሚዛን አማን ከተማ በፕሪሚየር ሊጉ ያደረጋቸውን ሁለት ጨዋታዎች የተሸነፈ ሲሆን በሊጉ የመጨረሻው ደረጃ ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ሦስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገም ቀጥለው የሚካሄዱ ሲሆን ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ከፌዴራል ፖሊስ እንዲሁም ባህር ዳር ከተማ ከከምባታ ዱራሜ ጋር ይጫወታሉ።

የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች በሦስተኛ ሳምንት የሊጉ መርሃ ግብር አራፊ ክለብ ነው።

የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከልና መቆጣጠር ፕሮቶኮልን መሰረት ባደረገ መልኩ በባህር ዳር፣ በሃዋሳና በአዲስ አበባ እንዲካሄድ መወሰኑ ይታወቃል።

በዚሁ መሰረት የፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያ አራት ሳምንት ጨዋታዎች በባህር ዳር እንዲከናወኑ በወጣው መርሃ ግብር መሰረት በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም በሚገኘው እጅ ኳስ ሜዳ ጨዋታዎች ያለተመልካች እየተካሄዱ ነው።

የመጀመሪያ ዙር ቀሪ ጨዋታዎች በሃዋሳና በአዲስ አበባ የሚካሄዱ ሲሆን በተመሳሳይ የሁለተኛ ዙር የፕሪሚየር ሊጉ ጨዋታዎች በሦስቱ ከተሞች እንደሚካሄዱ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም