ህብረተሰቡ በዓላትን ሲያከብር ከኮቪድ 19 ተገቢውን ጥንቃቄ እያደረገ መሆን እንዳለበት የጤና ሚኒስቴር አሳሰበ - ኢዜአ አማርኛ
ህብረተሰቡ በዓላትን ሲያከብር ከኮቪድ 19 ተገቢውን ጥንቃቄ እያደረገ መሆን እንዳለበት የጤና ሚኒስቴር አሳሰበ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 16 ቀን 2013 (ኢዜአ) ህብረተሰቡ በዓላትን ሲያከብር ከኮቪድ-19 ተገቢውን ጥንቃቄ እያደረገ መሆን እንዳለበት የጤና ሚኒስቴር አሳሰበ።
ሚኒስቴሩ በዓላቱን አስመልክቶ ከኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጋር መግለጫ ሰጥቷል።
የገና በዓል በያዝነው ወር መጨረሻ፣ የጥምቀት በዓል ደግሞ በቀጣዩ ወር ይከበራሉ።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ሳህረላ አብዱላሂ አንደገለጹት፤ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከፍተኛ የሆነ መንፈሳዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ስነ-ልቡናዊ ጫና እያደረሰ ይገኛል።
በኮቪድ-19 ቫይረስ የሚያዙና ህይወታቸውን የሚያጡ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱንም ገልጸዋል።
"የቫይረሱ ስርጭት እየጨመረ ከፍተኛ የጤና ስጋት ሆኖ ቀጥሏል" ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ ማህበረሰቡ በተለይ በዓላት ሲያከብር በጥንቃቄ መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ በበኩላቸው በመጪዎቹ በዓላት ምዕመናን ከኮቪድ-19 ለመጠበቅ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
"ወደ ቤተ እምነቶች ሲመጡ የአፍና የአፍንጫ ጭምብል ማድረግና ሌሎች የመከላከያ ዘዴዎችን በመጠቀም ራሳቸውንና ሌሎችን ከበሽታው መጠበቅ አለባቸው" ብለዋል።
አካላዊ ርቀትን በመጠበቅና ንክኪን በመቀነስ እንዲሁም ንጽህናን በመጠበቅ የወረርሽኙ ስርጭት እንዲቀንስ ማድረግ እንደሚገባ በመግለጽ ጥሪ አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ ከ1 ሚሊዮን 762 ሺህ 851 ሰዎች የኮቪድ ምርመራ የተደረገላቸው ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥም 121 ሺህ 399 ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል።እስካሁንም 1 ሺህ 882 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል።