ቀጥታ፡

ለውጭ ገበያ ለሚቀርቡና ከውጭ ለሚገቡ ምርቶች የጥራት ፖሊሲ እየተዘጋጀ ነው - ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር

ታህሳስ 16/2013 (ኢዜአ) ለውጭ ገበያ የሚቀርቡና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን የጥራት ደረጃ የሚያስጠብቅ ፖሊሲ እየተዘጋጀ መሆኑን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ። 

የንግድ ፍቃድ ምዝገባና እድሳት አገልግሎት ከአንድ ወር በኋላ በአገር አቀፍ ደረጃ በኦንላይን ሊሰጥ ነው።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ እሸቴ አስፋው ለኢዜአ እንደተናገሩት በአገር ውስጥ ተመርተው ወደ ውጭ የሚላኩ የኢትዮጵያ ምርቶችም ሆነ ከውጭ ለሚገቡት የጥራት ፖሊሲ በመሰናዳት ላይ ነው።

ፖሊሲው የወጪና ገቢ ምርቶችን ጥራት ለመጠበቅ እንደሚያስችልም አስረድተዋል።

በአገሪቷ 253 አስገዳጅ ደረጃዎች መውጣታቸውንና 11 ሺህ 200 የኢትዮጵያ ደረጃዎች መኖራቸውን የገለጹት አቶ እሸቴ እነዚህን ለማስጠበቅ ፖሊሲ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

"የምርት ደረጃ የዓለም ቋንቋ ነው፤ ጥራት ደግሞ ምርቶችን የትም አገር መሸጥ መለወጥ የሚቻልበትን ደረጃ መጠበቅ የሚያስችል ነው" ያሉት አቶ እሸቴ ከምርት እስከ ገበያ መዳረሻ ጥራትን ለማስጠበቅ የሕግ ማዕቀፉ እየተሻሻለ መሆኑን ጠቁመዋል።

የጥራት ደረጃ በማውጣትና የላቦራቶሪ አቅምን በማሳደግ ጥራታቸውን ያልጠበቁ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ወደመጡበት እየተመለሱ መሆኑንም ገልፀዋል።

በአገር ውስጥ ተመርተው የሚላኩ ምርቶችም ጥራታቸውን የጠበቁና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለማድረግ ይሰራል ብለዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው በአገር አቀፍ ደረጃ የንግድ ፍቃድ ምዝገባና እድሳት አገልግሎት ከአንድ ወር በኋላ በኦንላይን የመስጠት ስራ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንደሚሆንም አስታውቀዋል።

በተጨማሪም የንግድ እንቅስቃሴውን የሚጎትቱ የአሰራርና የሕግ ማዕቀፎች ዙሪያ ማሻሻያዎች እየተደረጉ መሆኑንም ገልጸዋል።

ከዚህም መካከል የንግድ ፖሊሲ ማዘጋጀትና የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ማሻሻያዎች መከናወናቸውን አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም