ቀጥታ፡

ሊዲያ ታፈሰ ከ20 አመት በታች የሴቶች ዓለም ዋንጫ ጨዋታዎችን እንድትዳኝ ተመረጠች

አዲስ አበባ ግንቦት 2/2010 ኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ የፊፋ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ዓለም ዋንጫ ጨዋታዎችን እንድትዳኝ ተመረጠች። በፈረንሳይ አስተናጋጅነት ለዘጠነኛ ጊዜ የሚከናወነው የፊፋ ከ20 አመት በታች የሴቶች ዓለም ዋንጫ ከሐምሌ 29 እስከ ነሐሴ 18 ቀን 2010 ዓ.ም ይካሄዳል። የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የዳኞች ኮሚቴ ውድድሩን እንዲመሩ ከ21 አገራት 15 ሴት ዋና ዳኞችና 30 ረዳት ዳኞችን ይፋ አድርጓል። በዚሁ መሰረት ኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ በዋና ዳኝነት ከተመሩጡት መካከል አንዷ ሆናለች። ሊዲያ ታፈሰ ፊፋ በውድድሩ እንዲያጫውቱ ከመረጣቸው የአፍሪካ አገራት ሁለት ዳኞች መካከል አንዷ ስትሆን ዛምቢያዊቷ ሌንግዌ ግላዲየስ ሌላኛዋ ውድድሩ ላይ እንድታጫውት የተመረጠች አፍሪካዊ ዳኛ ናት። ዳኞቹ የተመረጡት በአገራቸውና በአህጉር አቀፍ ውድድሮች ላይ ባላቸው ልምድና ብቃት እንዲሁም ባላቸው የአካል ብቃት ደረጃና የጨዋታ ማንበብ ክህሎት እንደሆነ ፊፋ አስታውቋል። አፍሪካ፣ አውሮፓ፣ እስያ፣ላቲን አሜሪካ፣ ሰሜን አሜሪካና ኦሺኒያ ዳኞቹ የተመረጡባቸው አህጉራት ሲሆኑ አውሮፓ አምስት ዋና ዳኞችን በማስመረጥ ቀዳሚውን ስፍራ ይዛለች። በአንጻሩ የኦሺኒያ አህጉር አንድ ዳኛ ብቻ ስታስመርጥ ሌሎቹ አህጉራት ሁለት ዳኞችን ማስመረጥ ችለዋል። ኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ ባለፉት ተከታታይ ዓመታት አህጉራዊ እና አለም አቀፍ ውድድሮች ላይ የማጫወት ልምድ አላት። ከሶስት ዓመት በፊት በካናዳ በተካሄደው የዓለም ሴቶች ዋንጫ እና የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ውድድሮች ላይ ጨዋታዎችን መምራት ችላለች። ሊዲያ ከሁለት ዓመት በፊት በዮርዳኖስ በተካሄደው ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ዓለም ዋንጫ ላይም ተመርጣ በውድድሩ የተካሄዱ ጨዋታዎችን መርታለች። ኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ የ2008 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ኮከብ ዳኛ ተብላ መመረጧም ይታወቃል። ፊፋ በሰኔ ወር 2010 ዓ.ም በሩሲያ አስተናጋጅነት በሚካሄደው የዓለም ዋንጫ ኢትዮጵያዊውን ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ እንዲያጫውት መምረጡ የሚታወስ ነው። በፈረንሳይ በሚካሄደው የፊፋ ከ20 አመት በታች የሴቶች ዓለም ዋንጫ 16 ቡድኖች ይሳተፋሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም