የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮችን ለመቋቋም በሳይንስ ዘርፍ በትጋት መስራት ይገባል ...ፕሮፈሰር ሂሩት ወልደማርያም - ኢዜአ አማርኛ
የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮችን ለመቋቋም በሳይንስ ዘርፍ በትጋት መስራት ይገባል ...ፕሮፈሰር ሂሩት ወልደማርያም
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 16/2013(ኢዜአ) የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮችን ለመቋቋም በሳይንስ ዘርፍ ተግቶ መስራት እንደሚገባ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ፕሮፈሰር ሂሩት ወልደማርያም ገለጹ።
የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ሳይንስ ካውንስል የምክክር መድረክ "ሳይንስ ለኢትዮጵያ ልማትና ብልፅግና" በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ ፕሮፈሰር ሂሩት ወልደማርያምን ጨምሮ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ እና ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።
ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ የምክክር መድረኩ በረቂቅ ደረጃ በተዘጋጀው የኢትዮጵያ የሳይንስ ፖሊሲና ስትራቴጂ ሰነድ ላይ በመወያየት ግብዓት ለመሰብሰብ መዘጋጀቱን ገልፀዋል።
ረቂቅ ሰነዱ የአገሪቷ ሳይንስ እንዴት መልማትና መምራት እንደሚቻል በዝርዝር የሚያሳይ እንደሆነም ተናግረዋል።
ለሰነዱ ማስፈፀሚያ የሚሆኑ ስድስት ፕሮግራሞች መዘጋጀታቸውንም ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል።
ብሔራዊ የሳይንስ ካውንስል ኢትዮጵያ በቀጣዮቹ 10 ዓመታት በምን አይነት አዋጭ የሳይንስ ተግባር መሰማራት እንዳለባትና ለሳይንስ በሚያስፈልጉ መሰረተ ልማትና የሰው ሀብት ላይ የሚመክር ነው ብለዋል።
በምክክር መድረኩ ካውንስሉን መምራት በሚያስችለው መመሪያ ላይ ውይይት እንደሚደረግም ጠቁመዋል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ መድረኩ በዋናነት ካውንስሉ በቀጣይ እንዴት መስራት እንዳለበትና የግንኙነት አግባብ ላይ የሚነጋገር ነው ብለዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ጉዳይ አማካሪ ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም 'ሳይንስ ዓለማችንንና አካባቢያችንን የምንገልፅበት መንገድ ስለሆነ ወጣቶችን በሳይንስና ቴክኖሎጂ ማሰልጠን ያስፈልጋል' ብለዋል።
በዓለም ላይ የሚከሰቱ የተለያዩ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የሚፈቱት በሳይንስ እንደሆነም ተናግረዋል።
ፕሮፌሰሯ 'የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮቻችንን ለመቋቋም በሳይንስ ዘርፍ ጠንክሮና ተግቶ መስራት ይገባል' ሲሉም ገልጸዋል።
ካውንስሉ 65 ተቋማት በአባልነት የሚገኙበት ሲሆን አገራዊ የሳይንስ ፖሊሲና ስትራቴጂ ቁልፍ ጉዳዮችን ከተቋማት ተልዕኮ ጋር በማቀናጀት ይሰራል።
የሳይንስ ልማትና ባሕል ግንባታ ስራን በማሳደግ ሁለንተናዊ እድገት ለማምጣት በሚደረገው ጉዞ የሳይንስን ድርሻ ለማጉላት የተቋቋመ ካውንስል እንደሆነም ተገልጿል።