ቀጥታ፡

ኢትዮጵያና የዓለም ባንክ የ100 ሚሊዮን ዶላር የብድር ስምምነት ተፈራረመ

አዲስ አበባ ታህሳስ 16 / 2013 (ኢዜአ) የብድር ስምምነቱ በኢፌዴሪ ገንዘብ ሚኒስትር ዴዔታ ያስሚን ወሀብሬቢ እና በዓለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን እና ኤርትራ ዳይሬክተር ኦስማን ዲዮን ተፈርሟል።

በስምምነቱ ወቅት ሚኒስትር ዴታዋ እንደተናገሩት ከዓለም ባንክ የተገኘው የ100 ሚሊዮን ዶላር የብድር በጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ የተሰማሩ ሴት ስራ ፈጣሪዎችን ለመደገፍና አዳዲስ የስራ እድል ለመፍጠር ያግዛል ።

በጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ የተሰማሩ ሴት ስራ ፈጣሪዎች የክህሎት ስልጠና አግኝተው ውጤት እንዲያስመዘግቡ ለማድረግ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ገልጸል።

አበዳሪ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትንና ጥቃቅንና አነስተኛ የንግድ ቢሮዎች የቴክኒክ ድጋፍ ለማድረግ እንደሚረዳቸውም አክለዋል።

የዓለም ባንክ ኢትዮጵያ የምታደርገውን የልማት ስራ ለመደገፍ ለሰጠው የፈጣን ምላሽም አመስግነዋል።

በዓለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን እና ኤርትራ ዳይሬክተር ኦስማን ዲዮን በበኩላቸው "ብድሩ በአነስተኛና ጥቃቅን ዘርፍ የተሰማሩ ኢትዮጵያዊያን ሴቶችን ለማገዝ የሚያስችል ነው" ብለዋል።

የተደረገው የብድር ስምምነትም በአነስተኛና ጥቃቅን ዘርፍ የተሰማሩ ሴቶች ክህሎታቸውን በማሳደግ፣ የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል፣ አዳዲስ የስራ እድል ለመፍጠርና ገቢን ለማሳደግ እንደሚስችላቸው አንስተዋል።

የዓለም ባንክ ኢትዮጵያ ስራ ፈጣሪ ሴቶችና ወጣቶችን ለማበረታታት የምታደርገውን ጥረት ለማገዝ የሚያደርገው ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስገንዝበዋል።

የብድር ስምምነቱ ከ38 ሺህ በላይ ሴት ስራ ፈጣሪዎችን ለመደገፍ የሚውል መሆኑንም አንስተዋል።

በአዲስ አበባ፣ ድሬ-ደዋ፣ መቐለ፣ አክሱም፣ ባህር-ዳር፣ ጎንደር፣ ሃዋሳ፣ ዲላ፣ አዳማ፣ አሰላ እና በመላ አገሪቱ በሚገኙ ሌሎች 89 የስራ አድል መፍጠሪያ ማእከላት (ሳተላይቶች) ተግባራዊ እንደሚሆኑ ተገልጿል።

ፕሮጀክቱ የገንዘብ እጥረት ያለባቸውን ጥቃቅንና አነስተኛ ድርጅቶች ብድር የሚያገኙበትን መንገድ ለማመቻቸት ብሎም ኮቪድ-19 በስራቸው ላይ ጫና ያሳደረባቸውን ሴቶች ለመደገፍ እንደሚያግዝ ተነግሯል።

በአገልግሎቱ ተጠቃሚ የሚሆኑ ስራ ፈጣሪ ሴቶችም ለመጀመሪያ ጊዜ ያለ ከፍተኛ ማስያዣ ብድር ለማግኘት እንደሚያስችላቸው ተነስቷል።

በአነስተኛና ጥቃቅን ዘርፍ የተሰማሩ ሴት ስራ ፈጣሪዎችን ለመደገፍ የካናዳ፣ ጣሊያን፣ የጃፓን መንግስትና እና የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ እገዛ ሲያደርጉ የቆዩ ሲሆን ወደ ፊትም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ታውቋል።


የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም