ማዕከላዊ የስምጥ ሸለቆ አካባቢን ቀዳሚ የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ እንደሚሰራ የኦሮሚያ ክልል ገለፀ - ኢዜአ አማርኛ
ማዕከላዊ የስምጥ ሸለቆ አካባቢን ቀዳሚ የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ እንደሚሰራ የኦሮሚያ ክልል ገለፀ
ታህሳስ 16 ቀን 2013 (ኢዜአ) 14 ሺህ 400 በላይ ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋት ያለውና ከአጠቃላይ የኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ ተፋሰስ 27 በመቶውን የሚሸፍነው የማዕከላዊ ስምጥ ሸለቆ አካባቢን ቀዳሚ የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ እንደሚሰራ የኦሮሚያ ክልል ገለፀ።የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ከበደ ደሲሳ “ኦሮሚያ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ እንዲሁም ባህላዊ የቱሪዝም ፀጋዎች የታደለ መሆኑን ከነዚህ መካከል ማዕከላዊ ስምጥ ሸለቆ አንዱ ነው” ብለዋል።
መካከለኛው ስምጥ ሸለቆ የክልሉን 90 በመቶ ሐይቆችን፣ የዱር እንስሳትን፣ ፓርኮች፣ ባህላዊና ታሪካዊ ቦታቸውን የያዘ ቦታ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
አካባቢውን ፀጋዎች በማልማትና በማስተዋወቅ ዘላቂ የቱሪዝም ማዕከል ለመገንባት ክልሉ ትልቅ ትኩረት መስጠቱን ተናግረዋል።
ለዚህም የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን መቋቋሙን ገልፀው፤ ለዚህ ደግሞ የባለድርሻ አካላት ትብብርና ቅንጅት እንደሚያሻ ገልፀዋል።
በቅርቡ የተቋቋመው የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ዳይሬክተር ወይዘሮ ሌሊሴ ዱጋ ትኩረት ሳይሰጠው የቆየውን የኦሮሚያ ቱሪዝም ለማስተዋወቅ ስራው በስምጥ ሸለቆ ቱሪዝም መዳረሻዎች ማልማትና ማስተዋወቅ መጀመሩን ተናግረዋል።
በዚህም ማህበረሰብ አቀፍ ቱሪዝም በመገንባት በክልሉ ለ500 ሺህ ሰዎች የስራ ዕድል ለመፍጠር መታቀዱንና በአገር ውስጥ ቱሪዝም በመገንባት ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።
በሰው ሰራሽ ችግሮች ብዝሃ ሕይወቱ የተጎዳውን የማዕከላዊ ስምጥ ሸለቆ በማልማትና በማስተዋወቅ በቱሪዝም ማርኬቲንግ ላይ በስፋት ለመስራት ከሚዲያዎች፣ ከሌሎች ክልሎችና ዓለምአቀፍ ድርጀቶች ጋር እንደሚሰራ ገልፀው፤ በኦሮሚያ ቱሪዝም ሀሳብ ያላቸውና ለመሳተፍ ለሚሹ አካላትም ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቧል።
የአብጃታ ሻላ፣ ላንጋኖና ዝዋይ ሐይቆችና የበርካታ ብዝሃ ሕይወት ባለቤት የሆነው የመካከለኛው ስምጥ ሸለቆ አካባቢ ለአዲስ አበባና ከሌሎች የኢኮኖሚ ማዕከላት ከተሞች ያለው ቅርበት፤ የተሻለ የመንገድና የሆቴል መሰረተ ልማት ተደራሽነትና በበርካታ አቅጣጫ የሚገናኝ ቦታ በመሆኑ ለአገር ውስጥና ለውጭ ቱሪዝም መዳረሻነት እምቅ አቅም እንዳለው ጠቁመዋል።
የስምጥ ሸለቆ አካባቢውን ዘላቂነት ያለው የቱሪዝም ልማትና መዳረሻ ለመገንባት የጋራ ግብረሐይል ዛሬ ይቋቋማል።
የስምጥ ሸለቆን ቱሪዝም ዘላቂነት ለማረጋገጥ ላይ ያተኮረ አገራዊ መድረክ በሻሸመኔ ከተማ እየተካሄ ነው።