ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነታችንን በማጠናከር የሚገጥሙንን ፈተናዎች በጋራ መክተን ማለፍ አለብን...አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ - ኢዜአ አማርኛ
ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነታችንን በማጠናከር የሚገጥሙንን ፈተናዎች በጋራ መክተን ማለፍ አለብን...አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ
ጂግጅጋ፤ታህሳስ 16/2013(ኢዜአ) በኢትዮጵያ እየገጠሙ ያሉ ፈተናዎችን በመመከት ለማሸነፍ ከመቼውም ጊዜ በላይ ዜጎች አንድነታቸውን በማጠናከር ማለፍ ይገባል ሲሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ተናገሩ።
የዴሞክራሲ ተቋማትም ለዜጎች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር በትኩረት መስራት ይኖርባቸዋል ብለዋል።
በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ለሶስት ቀናት የሚካሄደው የፌዴራል የዴሞክራሲ ተቋማት የጋራ ምክክር መድረክ ተጀምሯል።
በመድረኩ ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስራ ሃላፊዎች፣ የምክር ቤቱ የመንግስት ተጠሪዎችና የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች፣ የፌደራል የዴሞክራሲ ተቋማት ኃላፊዎች እንዲሁም የሶማሌ ክልል ከፍተኛ አመራሮች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እየተሳተፉ ይገኛል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ፤የለውጡ እውን መሆን ሕዝቡን ሲመዘብሩ የነበሩ ቡድኖች ጥቅማቸው መቅረቱን ተከትሎ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ዜጎች ላይ ጥቃት እየፈጸሙ መሆኑን ገልጸዋል።
በነዚህ ቡድኖች ሴራ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በንጹሃን ዜጎች ላይ እጅጉን አሳዛኝ ግድያ መፈፀሙን ጠቅሰው፤ የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በተለያየ ጊዜ የገጠሟትን ፈተናዎች በልጆቿ የተባበረ ክንድ ማለፏን ያወሱት አፈ-ጉባኤው ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነታችንን በማጠናከር የሚገጥሙንን ፈተናዎች መሻገር ይገባናል ብለዋል።
በተለይም የዴሞክራሲ ተቋማት ነጻና ገለልተኝነታቸውን ጠብቀው ለዜጎች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኢብራሂም ኡስማን በበኩላቸው የሶማሌ ክልል ከለውጡ በፊት በከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰትና በዜጎች ሰቆቃ የሚታወቅ እንደነበር አስታውሰዋል።
የለውጡ አመራር በወሰዳቸው ዘርፈ-ብዙ ማሻሻያዎች የክልሉ ችግር ደረጃ በደረጃ እየተፈታ መጥቷል ብለዋል።
በመድረኩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአምስት ዓመት ዕቅድ፣ የዴሞክራሲ ተቋማት ስላላቸው የስራ ግንኙነት ተቋማቱን ለማጠናከር በሚከናወኑ ተግባራት ዙሪያ እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የማሻሻያ ስራዎች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል።