በደቡብ ክልል የከተማ ምግብ ዋስትና መርሀ-ግብር ይፋ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ክልል የከተማ ምግብ ዋስትና መርሀ-ግብር ይፋ ተደረገ
ሀዋሳ ታህሳስ 15/2013 (ኢዜአ ) በደቡብ ክልል ከ79 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የከተማ ምግብ ዋስትና ሴፍቲ ኔት መርሀ-ግብር የፋ ተደረገ፡፡
መርሀ ግብር ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ይፋ በተደረገበት ወቅት በአለም ባንክ የከተማ ልማታዊ ሴፍቲ ኔት መርሀ-ግብር የኢትዮጵያ አስተባባሪ አቶ ደበበ ባሩድ እንዳሉት ከዚህ በፊት መርሀ-ግብሩ ተግባራዊ ሲደረግ የቆየው በገጠሩ የሀገሪቱ ክፍል ነበር፡፡
ከሁለት ዓመታት በፊት በ11 ከተሞች በሙከራ ደረጃ ተካሂዶ አበረታታች ውጤት መገኘቱን ጠቁመዋል።
መስራት እየቻሉ ከቤት የዋሉ ልዩ ድጋፍ የሚሹና በየጎዳናው የሚገኙ ዜጎች እንዲሁም አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አስረድተዋል።
ይህን መሰረት በማድረግ ለአምስት ዓመታት የሚቆይና በ72 ከተሞች ተግባራዊ የሚደረግ አዲስ የከተማ ሴፍቲ ኔት መርሀ ግብር መጀመሩን ጠቁመዋል።
መርሀ ግብሩ ከቀድሞዎቹ በተጨማሪ ወጣቶችን በሥልጠና እና በሥራ ዕድል ፈጣራ የሚደግፍ እንዲሁም ሰደተኞችን ተጠቃሚ የሚያደርግ አሰራር ማካተቱን አስተባባሪው ጠቅሰዋል፡፡
በደቡብ ክልል ከሚገኙ አሥር ዞኖች ውስጥ በ13 ከተሞች መርሀ-ግብሩ ተግባራዊ እንደሚደረግና በዚህም ከ79 ሺህ በላይ ዜጎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አቶ ደበበ አስታውቀዋል።
የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው በበኩላቸው መርሀ-ግብሩ ከዓለም ባንክ ድጋፍና በኢትዮጵያ መንግስት በሚመደብ በጀት ተግባራዊ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡
በውጭድጋፍና ብድር በሚገኝ ገንዘብ ተግባራዊ የሚደረጉ ፕሮጀክቶች ላይ የአጠቃቀም ክፍተትና ብክነት እንደሚስተዋል ጠቁመው አመራሩ ይህ እንዳይከሰት ተገቢውን ክትትልና ድጋፍ እንዲያደርግ አሳስበዋል።
ተጠቃሚ መሆን የሚገባቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን የመለየቱ ሥራ ፍትሐዊና ጥንቃቄ የተሞላበት መሆን እንደሚገባው አመልክተዋል፡፡
በልየታ ወቅት ሆን ተብሎ ለሚፈጠር ስህተት በማንኛውም ደረጃ ያለ አመራር ቢሆን አንታገስም ብለዋል።
የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ይገዙ ለመርሀ-ግብሩ መሳካት ባለድርሻ አካላት በተለየ ትኩረት መሥራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
በዚህ መርሀ-ግብር ላይ የአሰራር ክፍተት የሚፈጥሩ አካላትን ተጠያቂና የፈጸሙትን ችግር ለህዝቡ ይፋ የማድረግ ሥራም ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚተገበር አስታውቀዋል።
መርሀ-ግብሩ በርካታ ዜጎችን ተደራሽ የሚያደርግና የከተሞችን ነባራዊ ሁኔታዎች የሚቀይር ትልቅ ዕድል ይዞ የመጣ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ኢንተርፕራይዞችና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃለፊ አቶ ተሾመ ታከለ ናቸው።
ለስኬታማነቱ ሁሉም በሀላፊነት መስራት እንዳለበትም ጠቁመዋል።