ባህር ዳር ከተማ ጽዱና ለኑሮ ምቹ እንድትሆን እየተደረገ ያለውን ጥረት ነዋሪዎች እንዲያግዙ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
ባህር ዳር ከተማ ጽዱና ለኑሮ ምቹ እንድትሆን እየተደረገ ያለውን ጥረት ነዋሪዎች እንዲያግዙ ጥሪ ቀረበ
ባህር ዳር ታህሳስ 15/2013(ኢዜአ) ባህር ዳር ከተማ ይበልጥ ጽዱ ለኑሮ ምቹ እንድትሆን እየተደረገ ያለውን ጥረት ነዋሪዎች ተቀናጅተው እንዲያግዙ የከተማዋ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጥሪ አቀረቡ።
አመራሮችና ታዋቂ አርቲስቶች ጭምር የተሳተፉበት የከተማዋ የጽዳት ንቅንቄ መረሃ -ግብር ዛሬ በይፋ ተጀምሯል።
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሣህሉ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ የጽዳት ንቅናቄው በከተማ አስተዳደር ደረጃ በወር አንድ ጊዜ በክፍለ ከተሞች ደግሞ በወር ሁለት ጊዜ የሚካሄድ ይሆናል።
ከተማዋ በተፈጥሮ የታደለችና የበርካታ ጎብኝዎች መዳረሻ መሆኗን ጠቅሰው፤ባህርዳር በተፈጥሮ የተሰጣትን ውበት ለመጠበቅ በየአካበቢው የሚጣል ቆሻሻ ሥርዓት ባለው መንገድ ማስወገድ እንዲቻል ለኀብረተሰቡ ግንዛቤ መፍጠር እንደሚገባ ተናግረዋል።
ለዚህም መላው ነዋሪዎች የከተማዋን ውበት ለመጠበቅ ከዚህ ቀደም እያደረገ ትጋት የበለጠ አጠናክሮ ማገዙን እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
ባህርዳርን ውብና ማራኪነቷን አስጠብቆ አለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንድትሆን ለማስቻል የሁሉም ኀብረተሰብ ርብርብን እንደሚጠይቅ ገልጸዋል።
ባህር ዳርን የበለጠ ሳቢና ማራኪ ለማድረግ የከተማ አስተዳደሩ የጀመረው የንቅናቄ ስራ የሚያስመሰግን መሆኑን የገለጸው ደግሞ በመረሃ-ግብሩ የተሳተፈው አርቲስት ሰማኸኝ በለው ነው።
"የባህር ዳር ከተማ ተወልጀ ያደኩባትና ሁሉ ነገሬ ናት'' ያለው አርቲስቱ፤ ከተማዋን ለማጽዳትና ለማስዋብ ለሚደረጉ ተግባራት በሚችለው ሁሉ ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።
የባህር ዳር ከተማን በአግባቡ መያዝ ከተቻለ በዓለም ላይ አሉ ከሚባሉ ከተሞች ተወዳዳሪ ማድረግ እንደሚቻል የጠቀሰው አርቲስቱ፤ ለዚህ ደግሞ መተባበርና መተጋገዝ ያስፈልጋል ብሏል።
አርቲስት ጌቴ አንላይ በበኩሉ የባህር ዳር ከተማ ከውብ የአየር ንብረት ፀጋ ጋር በተፈጥሮ የታደላትና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ናት ሲል ገልጿል።
ይህንን ውበቷን አስጠብቆ ይበልጥ ለማሳመረ ተቀናጅቶ መስራት እንደሚገባ ጠቅሶ፤ለዚህም በሚችለው አቅም ሁሉ ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን ተናገሯል።
የአማራ ወጣቶች አረንጓዴ ፎረም ፕሬዝዳንት ወጣት በለጠ ወዳጅነው እንዳለው፤ የከተማዋን ጽዳትና ውበት ከመጠበቅ ባለፈ ወጣቱ በአስተሳሰብም ጽዱና ለዓላማ የሚኖር እንዲሆን በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።
ፎረሙ የባህርዳር ከተማን ጽዳትና ውበት ከማስጠበቅ በተጨማሪ ወጣቱን በማስተባበር የተለያዩ የአረንጓዴ ልማት ስራዎች ላይም በትኩረት እየሰራ መሆኑን አስረድቷል።
በመረሃ-ግብሩ የአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች፣ ታዋቂ አርቲስቶችና የከተማዋ ማህበረሰብ አባላት ተሳትፈዋል።