የአዲስ አበባ አስተዳደር ለከተማዋ ጽዳትና ውበት ቅድሚያ ሰጥቶ እንደሚሰራ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ አስተዳደር ለከተማዋ ጽዳትና ውበት ቅድሚያ ሰጥቶ እንደሚሰራ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ገለጹ
አዲስ አበባ ሐምሌ 13/2010 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለከተማዋ ጽዳትና ውበት ቅድሚያ በመስጠት እንደሰሚሰራ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ ተናገሩ። ምክትል ከንቲባው የረጲ የደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመጫን ጎብኝተዋል። በጉብኝቱ ወቅት ኢንጂነር ታከለ እንደተናገሩት ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎችን በአግባቡ በመጠቀም መስራት ከተቻለ አገሪቱን መቀየርና የተሻለ ደረጃ ላይ ማድረስ ይቻላል። የቆሻሻ ማስወገድ ስርዓቱን ዘመናዊ ማድረግ እንደሚገባ ያስገነዘቡት ኢንጂነር ታከለ ከተማዋን ንጹህና አረንጓዴ ለማድረግ ሁሉም መስራት እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል። የቆሻሻ ማስወገጃ ስርዓታችን ዘመናዊ የሚያደርገውን ረጲ የደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመጫ መጎብኘት ያስፈለገው ለከተማዋ የጽዳት ጉዳይ ቅድሚያ ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ ለማሳየት ነው ብለዋል። የኢትዮዽያውያን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ አንዳንድ አካባቢዎች የሚታየው ቆሻሻ የከተማነት ደረጃዋን ዝቅ የሚያደርጉ በመሆናቸው ጽዳቱን ለመጠበቅ በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል። የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቱ እየተጠናቀቀ በመሆኑ በጥቂት ቀናት ውስጥ ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምር የተናገሩት ምክትል ከንቲባው ፕሮጀክቱ ኃይል ከማመንጨት ባለፈ የከተማዋን ጽዳትና ውበት ለመጠበቅ ታስቦ የተቋቋመ መሆኑን ጠቁመዋል። የረጲ የደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመጫ ቀሪ ስራዎች በአፋጣኝ ተጠናቀው ወደስራ እንዲገባ ለማስቻል የከተማ አስተዳደሩ ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል። በኤሌክትሪክ አገልግሎትና በሌሎች ተቋማት በኩል ፕሮጀክቱ ያለበትን ችግር ለመፍታት ከተማ አስተዳደሩ የሚጠበቅበትን እንደሚሰራም ተናግረዋል። በካምብሬጅ ኢንዱስትሪና በቻይና ናሽናል ኤሌክትሪክ ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን በ434 ሚሊዮን 530 ሺህ 557 ብር ወጪ እየተገነባ ያለው ፕሮጀክቱ በቀን 1ሺህ 400 ቶን ቆሻሻ የመቀበል አቅም ይኖረዋል።