የቱሪዝም ሀብቶችን በማልማትና በማስተዋወቅ ለሀገር ኢኮኖሚ ጠቀሜታ ማዋል ይገባል ... ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ - ኢዜአ አማርኛ
የቱሪዝም ሀብቶችን በማልማትና በማስተዋወቅ ለሀገር ኢኮኖሚ ጠቀሜታ ማዋል ይገባል ... ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ
ታህሳስ 15/2013 (ኢዜአ) የቱሪዝም መስህብ ሀብቶችን በማልማትና በማስተዋወቅ ለሀገር ኢኮኖሚ ጠቃሚ እንዲሆን መስራት እንደሚገባ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ አስታወቁ።
በኦሮሚያ የቱሪዝም ዘርፍ ለሀገር ኢኮኖሚ ሊያበረክት በሚችልባቸው እድሎች ላይ ያተኮረ ዐውደ ጥናት ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሄዷል።
በመድረኩ የተገኙት የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ "እንደ ክልል ሆነ በሀገር ደረጃ እምቅ የቱሪዝም ሀብት አለን፤ ነገር ግን አለን ማለቱ ብቻ ተጨባጭ አቅም መፍጠር አይችልም" ብለዋል።
በክልሉ መንግስት ካቢኔ ውሳኔ የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን መቋቋሙን ያወሱት ፕሬዝዳቱ ኮሚሽኑ ከተቋቋመ ወዲህ በዘርፉ ያከናወናቸው በርካታ ተግባራት መኖራቸውን ተናግረዋል።
በክልሉ በቱሪዝም ዘርፍ ያለውን ሀብት በማልማትና በማስተዋወቅ ለሀገር ኢኮኖሚ ጠቀሜታ ማዋል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ለተግባራዊነቱ የኮሚሽኑና የሌሎች ባለድርሻ አካላት ሚና የላቀ መሆኑን አመላክተዋል።"ኮሚሽኑ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በዘርፉ ተጨባጭ አቅም ለመፍጠር መስራት አለበት" ብለዋል ።
የክልሉ መንግስት ለቱሪዝም ዘርፉ እድገት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል።
የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ኮሚሽነር ሌሊሴ ዱጋ በበኩላቸው ኮሚሽኑ የተቋቋመበት ሶስት አንኳር ዓላማዎች እንዳሉት አመላክተዋል።
የኮሚሽኑን ዓላማ እውን ለማደረግ ከፌደራልና ከክልል የዘርፉ መስሪያ ቤቶች፣ ከአስጎብኚ ድርጅቶች፣ ከኢትዮጵያ አየር መንገድና ከሌሎች የዘርፉ ተዋናዮች ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ አመላክተዋል።
የአውደ ጥናቱ ዓለዓማ በዘርፉ የተሰማሩ ባለድርሻ አካላት በትብብር ወደ ተጨባጭ ስራ እንዲገቡ የሚያስችል አቅም መፈጠር መሆኑን ጠቅሰዋል።
በዐውደ ጥናቱ "በ10 ዓመቱ የልማት እቅድ ውስጥ ቱሪዝም ያሉት እድሎ"፣ "ቀጣይነት ላለው የቱሪዝም እድገት የክልሎች ትብብ"፣ "ማህበረሰብ አቀፍ የኤኮ ቱሪዝም ማስተዋወቅና ጥቅሞቹ" እንዲሁም "ቱሪዝም በስራ እድል ፈጠራ ውስጥ ያለው ሚና" በሚሉት ርዕሶች ላይ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
በዐውደ ጥናቱ የቱር ኦፕሬተሮች፣ አርቲስቶች፣ የክልልና የፌደራል ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኅላፊዎች እንዲሁም የሆቴል ባለሀብቶች ተሳትፈዋል።