ቀጥታ፡

የአዲሱ ካቢኔ ሹመት ብቃትን፣ ከሙስና ነጻ መሆንን እና የህዝብ ተቀባይነትን መሰረት ያደረገ ነው - ዶክተር ሙሉ ነጋ

ታህሳስ 15/2013 (ኢዜአ) የአዲሱ ካቢኔ ሹመት ብቃትን፣ ከሙስና ነጻ መሆንን እና የህዝብ ተቀባይነትንና አመኔታን መሰረት ያደረገ መሆኑን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ሙሉ ነጋ ገለጹ፡፡

በትግራይ ክልል የተሾሙት የካቢኔ አባላት በይፋ ስራ መጀመራቸውን አስመልክቶ ዶክተር ሙሉ ነጋ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳሉት፤ በክልሉ መሾም ካለባቸው 16 የካቢኔ አበላት እስካሁን 11ዱ ተሹመው በይፋ ስራ ጀምረዋል፡፡

በአዲስ መልክ የተዋቀረው ካቢኔ አባላት ብቁ፣ ከሙስና የጸዱና በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው መሆናቸው የተመረጡበት መስፈርት እንደሆነም አብራርተዋል።

በካቢኔ አባላት ሹመቱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት መካተታቸውንም ተናግረዋል፡፡

በክልሉ ዞኖች ተመድበው ወደ ስራ በገቡት አመራሮች አመርቂ ውጤት መገኘቱን ገልጸው፤ በምስራቃዊ፣ ደቡባዊ፣ ማዕከላዊ እና የሌሎች ዞን አመራሮች ተመድበው ወደ ስራ መግባታቸውን ጠቁመዋል፡፡

ከህብረተሰቡ ጋር ደረጃ በደረጃ እየተካሄደ ባለው ውይይት ህዝቡ የጊዜያዊ አስተዳደሩን ተግባር በሚገባ በመረዳት አመራሮችን በመምረጥ ላይ እንደሚገኝ ዶክተር ሙሉ አመልክተዋል፡፡

የወደሙ የመሰረተ ልማቶችን በመጠገን ወደ ስራ ለማስገባት በተከናወነው ስራ በርካታ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ፣ የውሃ እና የቴሌኮሙንኬሽን አገልግሎት ማግኘት መጀመራቸውን አንስተዋል።

የመሰረተ ልማት ጥገናው በተጠናከረ መልኩ መቀጠሉን የገለጹት ዋና ስራ አስፈጻሚው፤ "የቀሩ አካባቢዎች በቅርብ ጊዜ አገልግሎት ያገኛሉ" ብለዋል።

በትግራይ ክልል ደፍርሶ የነበረውን ሰላምና ጸጥታ ለመመለስ በክልሉ ህዝባዊ ፖሊስ የማዋቀር ስራ መጀመሩንም ዶክተር ሙሉ አብራርተዋል፡፡

በተለይ በመቀሌ ከተማ የፖሊስ አባላትን መልሶ የማደራጀት እንቅስቃሴው በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም