በዜጎች ላይ እየተካሄደ ያለው ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት ኃላፊነት የማይሰማቸው የግጭት ነጋዴዎች ሴራ ነው.... ብልጽግና ፓርቲ - ኢዜአ አማርኛ
በዜጎች ላይ እየተካሄደ ያለው ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት ኃላፊነት የማይሰማቸው የግጭት ነጋዴዎች ሴራ ነው.... ብልጽግና ፓርቲ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 15/2013(ኢዜአ) በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተደጋጋሚ በዜጎች ላይ እየተካሄደ ያለው ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት የትኛውንም የህዝብ ክፍል የማይወክልና ኃላፊነት የማይሰማቸው የግጭት ነጋዴዎች ሴራ መሆኑን ብልጽግና ፓርቲ ገለጸ።
ፓርቲው በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ቡለን ወረዳ በንጹሃን ዜጎች ላይ ማንነትን መሰረት በማድረግ እየተካሄደ ያለውን ጥቃት አወገዘ።
ፓርቲው ማምሻውን ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው ዜጎችን በማንነት ለይቶ በማጥቃት ምንም አይነት የፖለቲካ ትርፍ ሊገኝ አይችልም፡፡
"በጨካኝ አረመኔ የጥፋት ኃይሎች" ጥቃት በንጹሃን ዜጎች ላይ እየደረሰ ላለው ጉዳት የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን በመግለጽ ለዘመናት ተከባብሮ ክፉና ደጉን አብሮ ያሳለፈን ህዝብ በማጋጨት ርካሽ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚጣጣሩ የውስጥም ሆነ የውጭ ኃይሎች የማይሳካላቸው መሆኑንም ጠቅሷል።
በዜጎች ላይ እየደረሰ ባለው ጥቃት ተሳትፎ ያላቸውንና ችግሩ እንዲፈታ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ባልተወጡ የስራ ኃላፊዎች ላይ ጥብቅ ፖለቲካዊ፣ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑንም አስታውቋል።
"ምንም አይነት የፖለቲካ ተሳትፎ የሌላቸውን ለፍቶ አዳሪ ንጹሃን ዜጎችን በማንነታቸው ብቻ" ለይቶ በማጥቃት ሀገርንና ህዝብን ወደ ትርምስ ለማስገባት ተቀናጅተው የሚንቀሳቀሱ የውስጥም ሆነ የውጭ ጨካኝ የጥፋት ኃይሎችን" እንደሚያወግም በመግለጫው ተመልክቷል።
በእነዚህ ኃይሎች ላይ የማያዳግም እርምጃ ተወስዶ የዜጎች ሰላምና ደህንነት እንዲጠበቅ ብልጽግና ፓርቲ አጥብቆ የሚታገል መሆኑንም ገልጿል።
በክልሉ በተደጋጋሚ በዜጎች ላይ እየተካሄደ ያለው ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት የትኛውንም የህዝብ ክፍል የማይወክልና ኃላፊነት የማይሰማቸው የግጭት ነጋዴዎች ሴራ መሆኑን መላው የሀገሪቱ ህዝቦች ሊገነዘቡ ይገባል ብሏል ፓርቲው በመግለጫው።