የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ለኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ሁለት አውቶቡሶችን ሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ለኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ሁለት አውቶቡሶችን ሰጠ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 15/2013 (ኢዜአ) የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን /ኢሲኤ/ ለኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ለሚከናወኑ አገልግሎቶች የሚውሉ ሁለት አውቶቡሶች ድጋፍ አደረገ።
ለኮቪድ-19 ድንገተኛ ጊዜ ማመላለሻ እንዲያገለግሉ ተብለው የተበረከቱት አውቶቡሶች ርክክብ ተከናውኗል።
የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አስቻለው አባይነህ በቅርቡ በተሸከርካሪ እጥረት ምክንያት የሕክምና ባለሙያዎችን በተገቢው ሁኔታ ስራ ላይ ለማሰማራት ችግር ማጋጠሙን አስታውሰዋል።
በዚህ ሳቢያም ተቋሙ ለጤና አጠባበቅ ተመድቦ የነበረውን በጀት ለሠራተኞች የተሽከርካሪ ኪራይ ለማዋል ተገዶ እንደነበረም ጠቅሰዋል።
"በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን በኩል የተደረገው የተሽከርካሪ ድጋፍ ተቋሙ በጀቱን በአግባቡ ለመጠቀም እንዲሁም ያልተፈለጉ ወጪዎችን በማስቀረት እቅዶቹን በብቃት ለማሳካት ያግዘዋል" ብለዋል።

በተለይ ተቋሙ ለተሽከርካሪ ኪራይ የሚያወጣውን ወጪ እንደሚያስቀርለት የገለጹት አቶ አስቻለው ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
እንደ አቶ አስቻለው ገለጻ ኢትዮጵያ የሎጂስቲክስ አቅሟን በማሳደግ የሕክምና ግብዓት የተሟላለት አገልግሎት ለዜጎች የማቅረብ ሂደት እያጠናከረች ነው።
የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የአስተዳደራዊ ዘርፍ ዳይሬክተር ካርሎስ ሀዳድ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በዓለም ላይ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳድሯል ብለዋል።
"ወረርሽኙና በወረርሽኙ ሳቢያ እየጨመረ የመጣው የሟቾች ቁጥር ዓለምን በከፍተኛ ሁኔታ ላለመረጋጋት እየዳረጓት ይገኛሉ" ነው ያሉት።
በዓለም አቀፉ ወረርሽኝ ምክንያት የአገራትና የዜጎች ኢኮኖሚ ከፍተኛ ጫና ውስጥ መግባቱን የተናገሩት ዳይሬክተሩ በዚህ ወቅት የታየው ዓለም አቀፋዊ ትብብርና መደጋገፍ እንደሚደነቅ ገልጸዋል።
በወረርሽኙ ሳቢያ ለኅብረተሰቡ ጤና የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ አስፈላጊ መሆኑንም ነው የገለጹት።