ጡረተኞቹ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እየተሳተፉ ለሚገኙ ዜጎች የ579 ሺህ ብር ቦንድ በስጦታ አበረከቱ - ኢዜአ አማርኛ
ጡረተኞቹ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እየተሳተፉ ለሚገኙ ዜጎች የ579 ሺህ ብር ቦንድ በስጦታ አበረከቱ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 15/2013 (ኢዜአ) ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት በጡረታ የተሰናበቱ ሴቶች በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እየተሳተፉ ለሚገኙ ሴቶችና ለመከላከያና ፖሊስ ሠራዊት አባላት የ579 ሺህ ብር የቦንድ ስጦታ አበረከቱ።
በቦንድ ርክክቡ ላይ የሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስትሯ ፊልሰን አብዱላሂ እና የመከላከያ ኢንዶክትሪኔሽን ኃላፊ ሜጀር ጄኔራል መሃመድ ተሰማ ተገኝተዋል።
የቦንድ ስጦታ ሽልማቱ በተለይም በግድቡ ግንባታ ላይ እየተሳተፉ ለሚገኙ 429 ሴቶች ለእያንዳንዳቸው የአንድ ሺህ ብር የቦንድ ግዥ በአጠቃላይ 429 ሺህ ብር የሚያወጣ ነው።
ሚንስትሯ ፊልሰን አብዱላሂ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሲጠናቀቅ በሴቶች ላይ ያለውን የስራ ጫና በመቀነስ የበለጠ ተጠቃሚ ያደርጋቸዋል ሲሉ ተናግረዋል።
በራሳቸው ተነሳሽነት ድጋፍ ያደረጉትን ሴቶች አመስግነው ሴቶች በአገሪቷ ዕድገት በሁሉም መስክ እያደረጉ ያለውን ተሳትፎ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የሕዳሴው ግድብ እውን መሆን ለአገሪቷ ዕድገት ከሚያስገኘው ጥቅም ባሻገር የሕዝቦቿን ሕይወት ወሳኝ በሆነ መልኩ የሚለውጥ መሆኑን ገልጸዋል።
ሜጀር ጄኔራል መሃመድ ተሰማ በበኩላቸው ሴቶች በመከላከያ ሠራዊቱ ውስጥ ተሰልፈው ጁንታውን በማስወገድ ዘመቻ ላይ ያሳዩት ጀግንነት የሚደነቅ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በአገሪቷ ልማትም የሴቶች ተሳትፎ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል።
የአገር አንድነት በማስጠበቅ ሕዝቦቿም አኩሪ ታሪካቸውን እያደሱ እንዲቀጥሉ ዘላቂ ሠላም ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
የቦንድ ስጦታው የሕዳሴውን ግድብ በመጠበቅ ላይ ለሚገኙና በግንባታውም ላይ የተሰማሩ ሴቶችን ለማበረታታት የተበረከተ መሆኑን የስጦታው አስተባባሪ ወይዘሮ ሰብለ ደመቀ ተናግረዋል።
ስጦታው በግድቡ ላይ አሻራቸውን ለማሳረፍና በግንባታ ስራው ላይ የሚገኙ ሴቶች የሞራል ስንቅ እንዲሆናቸው የተበረከተ መሆኑን ተናግረዋል።
ሴቶቹ ግድቡን እየጠበቁ ለሚገኙ የመከላከያ ሠራዊትና የፌዴራል ፖሊስ አባላት እንዲሁም ለሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ለእያንዳንዳቸው የ50 ሺህ ብር ቦንድ በስጦታ አበርክተዋል።
ለግንባታው ተቋራጭ ሳሊኒ ኩባንያ ደግሞ የኢትዮጵያን ሴቶች የሚወክል ስዕል አበርክተዋል።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር አረጋዊ በርሄ ሕዝቡ ለግድቡ እያደረገ ያለው ድጋፍ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።
ግድቡ ከፍጻሜ እንዲደርስ ሕዝቡ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።
ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት ለግድቡ ግንባታ በቦንድ ግዥና በስጦታ ከ14 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ መገኘቱን ገልፀዋል።