የአጎራባች አገራት አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚሳተፉበት ኤግዚቢሽንና ባዛር ሊካሄድ ነው

66

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 15/2013 (ኢዜአ) ከአገር ውስጥና ጎረቤት ሀገራት 160 አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚሳተፉበት ኤግዚቢሽንና ባዛር በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው።

የፌዴራል አንስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል ኦላኒ እንደገለጹት በኤግዚቢሽኑ ከአጎራባች ሀገራት፣ አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማን ጨምሮ በክልሎች የሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎች ይሳተፋሉ።

ከአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ፣ ሲዳማ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ሐረሪ ከልሎች ተሳታፊዎች ናቸው ተብሏል።

በቆዳ፣ ጨርቃ ጨርቅ፣ አግሮ-ፕሮሰሲንግ፣ ኬሚካል፣ በእደ ጥበብ እና በቴክኖሎጂ ዘርፎች የተሰማሩ 132 አምራች ኢንዱስትሪዎች እንደሚሳተፉ ታውቋል።

ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ 26 ተሳታፊዎችም በባዛሩ ላይ የሚሳተፉ ሲሆን ቀሪ ሁለቱ ከጎረቤት ሀገራት ሱዳንና ጅቡቲ የሚመጡ መሆናቸውን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

በኤግዚቢሽኑ ሸማቾችና በተለይ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ አምራች የሆኑ ኢንዱስትሪዎች እርስ በርስ የሚገናኙበት ይሆናል ተብሏል።

መድረኩ አምራች ኢንዱስትሪዎች ምርቶቻቸውን ይዘው በመቅረብ እርስ በእርስ እንዲተዋወቁና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲያደርጉ ጭምር ታስቦ የሚዘጋጅ መሆኑንም ነው የገለጹት።

በኤግዚቢሽንና ባዛሩ ላይ እንዲሳተፉ የተመረጡ አምራቾች በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ባላቸው የቴክኖሎጂ ደረጃና በሀብት መጠናቸው የተሻሉ ሆነው በሞዴልነት የተመረጡ ናቸው።

ኤግዚቢሽንና ባዛሩ ከታህሳስ 21 እስከ 27 ቀን 2013 ዓ.ም የሚካሄድ መሆኑም ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም