ድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎችና ረዳቶቻቸው የሕይወት መድህን ተጠቃሚ ይሆናሉ - ኢዜአ አማርኛ
ድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎችና ረዳቶቻቸው የሕይወት መድህን ተጠቃሚ ይሆናሉ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 15/2013(ኢዜአ)ድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎችና ረዳት አሽከርካሪዎች ከዛሬ ጀምሮ የኮሮና ቫይረስ የሕይወት ኢንሹራንስ ሽፋን እንደሚገባላቸው ተገለፀ።
ጉዳዩን አስመልክቶ የመድን ፈንድ አስተዳደር ኤጀንሲ፣ የኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ሰጪዎች ማኅበርና የትራንስፖርት አሰሪዎች ፌዴሬሽን የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
የመድህን ሽፋኑ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ሕይወታቸውን ለሚያጡና ከስራ ገበታቸው ለሚርቁ አሽከርካሪዎችና ረዳቶቻቸው የሚከፈል ነው።
በዚህም አሽከርካሪዎች በቫይረሱ ምክንያት ሕይወታቸው ቢያጡ 250 ሺህ ብር ለረዳት አሽከርካሪዎች ደግሞ 150 ሺህ ብር ካሳ የሚከፈል ይሆናል።
በቫይረሱ ተጠቅተው ከስራ ለሚቀሩ አሽከርካሪዎችና ረዳት አሽከርካሪዎች በደመወዝ መልክ 6 ሺህ ብርና 3 ሺህ ብር ለሁለት ወር እንደሚከፈላቸው ተገልጿል።
ሽፋኑን ለመፈጸም ከብሔራዊ ባንክ ፍቃድ የተሰጣቸው ስምንት የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ለአገልግሎቱ ዝግጁ መሆናቸው ተነግሯል።
የመድህን ፈንድ አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተሯ ወይዘሮ ወርቅነሽ ብሩ ለአሽከርካሪዎች የሕይወት ኢንሹራንስ ለመግባት የአሜሪካ፣ የእንግሊዝ፣ የደቡብ አፍሪካና የሕንድ ተሞክሮ ተዳሷል።
አሽከርካሪዎች በእንቅስቃሴያቸው ወቅት የቤተሰባቸው ሁኔታ ስለሚያሳስባቸው የመድህን ሽፋኑ ያለባቸውን ስጋት ያቃልልላቸዋል ብለዋል።
በተለይም የኢኮኖሚው ዋና አንቀሳቃሽ የሆነው የገቢና ወጪ እንቅስቃሴ በኮሮና ቫይረስ እንዳይስተጓጎል ሽፋኑ አዎንታዊ ሚና እንዳለው ገልጸዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሯ አሽከርካሪዎች ሲንቀሳቀሱ ኢንሹራንስ የገቡበትን የምስክር ወረቀት መያዝ እንደሚኖርባቸው አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ሰጪዎች ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ነጻነት ለሜሳ በበኩላቸው የመድህን ሰጪ ተቋማት በተናጠል ድጋፍ ሲያደርጉ እንደነበረ አስታውሰው በማኅበር ደረጃ ይህ የመጀመሪያው ነው ብለዋል።
ለአሽከርካሪዎች የተደረገው የሕይወት ዋስትና ሽፋን አገልግሎቱ በኅብረተሰቡ ዘንድ እንዲለመድ ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
የመድህን ሽፋኑን የሚሰጡ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የሚሰጡት የምስክር ወረቀት ወጥ በሆነ መልኩ እየተዘጋጀ መሆኑንም አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ትራንስፖርት አሰሪዎች ፌዴሬሽን ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደጀኔ ሉጬ አሽከርካሪዎች የሕይወት ኢንሹራንስ እንዲገባላቸው ሲያቀርቡት የነበረው ጥያቄ ምላሽ ማግኘቱን ተናግረዋል።
በገላፊና ደወሌ የሚካሄደው የተሽከርካሪ ኬሚካል ርጭትና አሽከርካሪዎችን ሙቀት የመለካት ስራዎች ሊጠናከሩ እንደሚገባም ነው አጽንኦት የሰጡት።
የአሽከርካሪዎችና ረዳት አሽከርካሪዎች ኢንሹራንስ ሽፋኑ ለአንድ ዓመት የሚቆይ መሆኑን የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።