ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ እና የሱዳን ወሰን አካባቢ የተከሰተው ግጭት የሁለቱ አገራትን ሕዝቦች እና መንግስታት አይወክልም... ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት

ታህሳስ 15/2013(ኢዜአ) በኢትዮጵያ እና የሱዳን ወሰን አካባቢ የተከሰተው ግጭት በሁለቱ አገራት ሕዝቦች መካከል ጥርጣሬ እና ግጭት እንዲፈጠር ድብቅ አጀንዳ ይዘው የሚንቀሳቀሱ አካላት ሴራ መሆኑን መንግስት አስታወቀ::

ክስተቱን አስመልክቶ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት በአረብኛ ባወጣው መግለጫ የተፈጠረው ችግር የኢትዮጵያም ሆነ የሱዳን መንግስት ፍላጎት አይደለም ብሏል::

እንዲያውም በሁለቱ አገራት ሕዝቦች መካከል ጥርጣሬ እና ግጭት እንዲፈጠር ድብቅ አጀንዳ ይዘው የሚንቀሳቀሱ አካላት ሴራ መሆኑን እንገነዘባለን ብሏል::

ይሁን እንጂ ሁለቱ አገራት ችግሩን በጋራ በሠላማዊ ውይይት ለመፍታት ጥረት እንደሚያደርጉ የኢትዮጵያ መንግስት አስታውቋል::

ግጭቱ መፈጠሩ አሳዛኝ ቢሆንም በተለይም የኢትዮጵያ መንግስት በሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍል ሕግ የማስከበር ስራውን አጠናቆ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት እያከናወነ ባለበት ወቅት እና በተመሳሳይ መልኩ ሱዳን ደግሞ በህዝባዊ ተቃውሞ የተነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ ደፋ ቀና በምትልበት ጊዜ መፈጠሩ የበለጠ አሳዛኝ እንደሚያደርገው የኢትዮጵያ መንግስት ባወጣው መግለጫ አመልክቷል::

በሱዳንና ኢትዮጵያ ድንበር አካባቢ የተከሰተው የፀጥታ ችግርም የኢትዮጵያ ህዝብ እና መንግስትን የሚመጥንና የሚወክል አለመሆኑንም መግለጫው አስታውቋል::

ለዘመናት የዘለቀው ሁለቱ አገራት እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በሴረኞች እንደማይሰናከል የገለፀው መግለጫው፣ የሁለቱ አገራት ህዝቦች ነጻነታቸውን ከማረጋገጥ ባሻገርም፣ ከራሳቸው አልፈው ለአካባቢውም ጭምር ስልጣኔና ቅርስ አበርክቷቸው በጋራ የሚያስተሳስራቸው መሆኑም ተመልክቷል::

ይህም በሁለቱ አገራት እና ሕዝቦች መካከል ያለውን ወንድማዊ ግንኙነት የሚያሳይ መሆኑንም መግለጫው ማመልከቱን የኢብኮ ዘገባ ያሳያል።

ይሁን እንጂ በቅርቡ አንዳንድ አካላት በኢትዮጵያ እና ሱዳን መካከል ግጭት ለመፍጠር የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ የኢትዮጵያ መንግስት በቅርበት እየተከታተለው መሆኑን አስታውቋል::

ድርጊቱንም ሁለቱ አገራትን የማይወክል እና የተፈጠረውን ችግር በሠላማዊ ውይይት እንደሚፈቱት የኢትዮጵያ መንግስት አቋሙን ገልጿል::

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም