ቀጥታ፡

የእግር ኳስ ዳኞች ከነገ ጀምሮ ወደ መደበኛ ስራቸው ለመመለስ ተስማምተዋል

አዲስ አበባ ግንቦት 2/2010 የኢትዮጵያ እግር ኳስ ዳኞች አቋርጠውት የነበረውን የመዳኘት ስራ ነገ ለመጀመር መወሰናቸውን አስታውቀዋል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ዳኞችና ታዛቢዎች ማህበር በዳኞች ላይ የሚፈጸመው ጉዳት እየተባባሰ መጥቷል በሚል ቅሬታ  ሚያዝያ 24 ቀን 2010 ዓ.ም ጠቅላላ ጉባኤውን ባካሄደበት ወቅት ለሶስት ሳምንታት የትኛውንም ውድድር እንደማያጫዉቱ ባወጡት ባለ 10 ነጥብ የአቋም መግለጫ አስታውቀው ነበር። ይሁን እንጂ  ማህበሩ ዛሬ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር ባደረገው ውይይት "በማህበሩ አቋም መግለጫ የተነሱት ጥያቄዎች ከሞላ ጎደል ምላሽ በማግኘታቸው" ዳኞች ነገ ስራቸውን ለመጀመር መወሰናቸውን ገልጿል። "ሁሉም የዳኞች ጥያቄ ባይመለሱም በውይይቱ ላይ በማህበሩ የቀረቡ ጥያቄዎች በአጭር ጊዜ ሳይሆን በጊዜ ሂደት በፌደሬሽኑ የሚመለሱ መሆናቸው ከመግባባት ላይ መደረሱን" ማህበሩ አስታውቋል። ዳኞች ውድድር እንደማያካሄዱ በመግለጻቸው ምክንያት የ23 ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር አልተካሄደም። የዳኞች ማህበር ሚያዝያ 24 ቀን 2010 ዓ.ም ባደረገው ጠቅላላ ጉባኤ ወደ ውድድር ለመመለስ 10 ቅድመ ሁኔታዎች እንዲተገበሩ አስቀምጦ ነበር። እነዚህም ከዚህ በታች የተጠቀሱት ናቸው። በ2010 ዓ.ም የውድድር ዘመን የተጎዱ ዳኞች ተገቢው ካሳ እንዲሰጣቸው፣ ውድድሩን ከመጀመራችን በፊት በውድድር ደንቡ መሰረት የመድህን ዋስትና (ኢንሹራንስ) እንዲገባልን፣ ረዳት ዳኛ ሙስጠፋ መኪ በሃገር ውስጥም ሆነ ውጭ ሃገር ተገቢውን ህክምና እንዲያገኙ፤ ከክልል ፀጥታ አካላት ጋር በመግባባት የዳኞች ጥበቃ እንዲደረግ፣ በወንዶች እና በሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ለመዳኘት በሚደረግ ጉዞ አውሮፕላን የሚደርስበት ቦታ ሁሉ የአውሮፕላን ትራንስፓርት እንዲመቻች፣ የአልቢትር እያሱ ፈንቴን ጉዳይ ጨምሮ ፖሊስ ያወቃቸው የስርዓት አልበኝነትና የመብት ጥሰቶች ተገቢውን የህግ ፍርድ እንዲያገኙ እንዲደረግ፤ ፌዴሬሽኑ ለዳኞች እና ለታዛቢዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲያመቻች፣ ማህበሩ ያለአግባብ ለጠቅላላ ጉባኤ ያወጣው ወጪ በፌዴሬሽኑ በህጋዊ ደረሰኝ አማካኝነት እንዲመለስ፣ የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴዎቹ አሰራር በግልፅ እንዲጠየቅ እና ተገቢው የህግ ከለላ በሌለባቸው ስታዲየሞች ውድድር እንዳይካሄድ የሚሉ ናቸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም