ቀጥታ፡

የሥራ ላይ አደጋዎችና የሙያ ጉዳቶች እየጨመሩ ነው - የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 15/2013 ( ኢዜአ) ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውሉ ጥሬ ዕቃዎችና መሳሪያዎች በሚያስከትሉት ጫና የሥራ ላይ አደጋዎችና የሙያ ጉዳቶች እየጨመሩ መምጣታቸውን የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለፀ።

ሚኒስቴሩ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ትምህርት ቤት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የባለድርሻ አካላት ውይይት እየተካሄደ ነው።

በውይይት መድረኩ የተገኙት የአሠሪና ሠራተኛ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አየለች እሸቴ የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ልማት ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።

ይህን ተከትሎም ለኢንዱስትሪ ግብዓትነት የሚውሉ ጥሬ ዕቃዎችና መሳሪያዎች በሚያስከትሉት ዘርፈ ብዙ ጫና ምክንያት የሥራ ላይ አደጋዎችና የጤና ጉዳቶች እየተበራከቱ ይገኛሉ።

ለዚህም ለጥንቃቄ ያለው የግንዛቤ ማነስ፣ የሥራ አካባቢዎች ደረጃቸውን ያልጠበቁ መሆን እንዲሁም የሕግ አፈጻፀም ክፍተት ምክንያቶች መሆናቸውን ዘርዝረዋል።

"አሠሪዎች ለሙያ ደህንነትና ጤና ያላቸው አመለካከትና ትኩረት አነስተኛ መሆን፣ የሥራ ላይ አደጋዎችና የሙያ ጉዳቶች ጥናትና መረጃ አያያዝ እንዲሁም የሪፖርት ሥርዓት አለመጠናከር የሚጠቀሱ ናቸው" ብለዋል።

እነዚህ ምክንያቶች "በኢትዮጵያ ምቹ የሥራ ሁኔታ በመፍጠር ከአደጋ የተጠበቀ ጤናማ አምራች ኃይል እንዲኖር የማድረጉ ጥረት በሚፈለገው መጠን ግቡን እንዳይመታ አድርጎታል" ብለዋል ሚኒስትር ዴኤታዋ።

በብሔራዊ ደረጃ የሥራ ላይ አደጋዎችና የሙያ ጉዳቶችን ለመከላከልና ለመቀነስ የአሰሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅን የማሻሻል ሥራ መሰራቱንም ጠቁመዋል።

የማስፈፀሚያ መመሪያዎችን የመከለስና የሙያ ደህንነትና የጤና ፖሊሲና ስትራቴጂን ይበልጥ ተግባራዊ የማድረግ ሥራ እየተሰራ መሆኑንም አክለዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሕብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ትምህርት ቤት ዲን ፕሮፈሰር ደመን ኃይለማርያም በኢትዮጵያ በሥራ ላይ የሚደርሱ አደጋዎችና የሙያ ጉዳቶች በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመሩ መሆኑን አንስተዋል።

የሥራ ላይ አደጋዎችን ለመከላከልና ለመቀነስ የሰለጠነ የሰው ኃይል ማፍራት፣ የሕግ ማሻሻያ ማድረግ፣ የሠራተኞችን ግንዛቤ ማሳደግና የመረጃ አሰባሰብና የሪፖርት ሥርዓትን ማጠናከር ይገባል ብለዋል። 

"የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት በኩል የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ትምህርት ክፍል በተለያየ መርሃ ግብር ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ ይገኛል" ሲሉ ጠቁመዋል።

የውይይት መድረኩ የሥራ ላይ ጤና ጉዳዮች ምዝገባ፣ አደረጃጀትና የሪፖርት ስርዓት ጀረጃውን በጠበቀ ሁኔታ ለማከናወን ያሉትን ተግዳሮቶች በመለየት ማሻሻያ ስልቶችን ለመንደፍ ይረዳል ተብሏል።

በመድረኩ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸውም ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም