በመዲናዋ የድምፅ ብክለት የፈጠሩ 13 አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ታሽገዋል - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ የድምፅ ብክለት የፈጠሩ 13 አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ታሽገዋል
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 15/2013 ( ኢዜአ) በአዲስ አበባ ባለፉት ስድስት ወራት በድምፅ ብክለት ላይ በተደረገ ክትትልና ቁጥጥር 13 አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መታሸጋቸውን የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃና አረንጓዴ ልማት ኮሚሽን አስታወቀ።
ኮሚሽኑ በ167 አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ባደረገው ክትትልና ቁጥጥር በሚፈጥሩት የድምፅ ብክለት ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው ማስተካከያ ባላደረጉት ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታውቋል።
የድምፅ ብክለት በሰው ልጆች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድር፤ ጤናማ አካባቢን በማወክ በማኅበረሰብ ስነ-ልቦናዊና አካላዊ ጤንነት ላይም ጉዳት የሚያደርስ ነው።
የድምፅ መጠን እንደ ሰሚው ዕድሜ፣ የጤንነት ሁኔታ፣ እንደ ድምፁ ዓይነት፣ ቆይታና ድግግሞሽ የሚለያይ በመሆኑ ለአንዱ መደበኛ የሆነው ድምፅ ሌላውን የሚረብሽ ሆኖ የሚገኝበት ሁኔታ ይስተዋላል፡፡
የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃና አረንጓዴ ልማት ኮሚሽን ካሉት የስራ ክፍሎች መካከል የአካባቢ ብክለትና አየር ንብረት ለውጥ ክትትልና ቁጥጥር አንዱ ነው፡፡
ይህ ክፍል የድምፅም ሆነ የፍሳሽ አካባቢያዊ ብክለት በሚያስከትሉ አካላት ላይ ቁጥጥርና ክትትል ያደርጋል፡፡
የድምፅ ብክለትን የሚቆጣጠሩ ባለሙያዎቹም በምሽት ጭፈራ ቤቶች በመዘዋወር የድምፅ ልኬት እንደሚያደርጉ የኮሚሽኑ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሙክታር ሰኢድ ለኢዜአ ገልፀዋል፡፡
አቶ ሙክታር የድምፅ ብክለትን በተመለከተ ከኅብረተሰቡ በሚደርስ ጥቆማም ክትትልና ቁጥጥር ይደረጋል ይላሉ።
የድምፅ ብክለትን ለመከላከል በዴሲማል መሳሪያ ልኬት መሰረት የተቀመጠው የድምፅ መጠን 40 መሆኑንና ከዚህ መብለጥ እንደሌለበት ነው የተናገሩት፡፡
የተቀመጠውን መስፈርት አልፈው የሚገኙ ተቋማት፣ የመጠጥና የጭፈራ ቤቶች፣ ሬስቶራንቶች ማስጠንቀቂያ እንደሚሰጣቸው ገልጸዋል፡፡
የተሰጣቸውን ማስጠንቀቂያ ተቀብለው በማያስተካክሉ ላይም ተቋሙ አስተዳደራዊ እርምጃ እየወሰደ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡
በመዲናዋ ከድምፅ ብክለት ጋር በተያያዘ ክትትልና ቁጥጥር ተደርጎ ማስጠንቀቂያ ቢሰጣቸውም ማስተካከያ ባለማድረጋቸው እርምጃ የተወሰደባቸው 13 የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትን በዝርዝር አስቀምጠዋል።
1.ኤልቤስትሮ ባርና ሬስቶራንት
2. ዊንክ ላውንጅ
3.ሚሚስ አዲስ ባርና ሬስቶራንት
4.ፋርመርስ ማርኬት
5.አዲናስ ባርና ሬስቶራንት
6.ሴራኒ ባርና ሬስቶራንት
7.ሮያል ባርና ሬስቶራንት
8.ፋልከን ላውንጅ
9.ሰለሞን ጀርመን ሀውስ
10.ከዚራ ባርና ሬስቶራንት
11.ተክለኃይማኖት ግሮሰሪ
12.ዲ.አር.ቢ እምነበረድ ፋብሪካ እና
13.ቤስፖ ኤሌክትሮ መካኒካል ሰርቪስ ባለፉት ስድስት ወራት የማሸግ እርምጃ የተወሰደባቸው ናቸው ብለዋል።
ዳይሬክተሩ የታሸጉት ተቋማት ተገቢውን ቅጣት ከተቀጡ በኋላ ስለ ድምፅ ብክለት ግንዛቤ እንዲኖራቸው በማድረግ ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።