ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ መንግስት በትኩረት እየተሰራ ነው- አቶ አዲሱ አረጋ

ጎባ፣ ታህሳስ 15/2013( ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል መሠረታዊ የጤና አገልግሎትን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ መንግስት በትኩረት እየሰራ መሆኑን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ አዲሱ አረጋ ገለጹ።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የሥራ ሃላፊዎች በባሌ ዞን በመንግሥትና ህብረተሰቡ ተሳትፎ እየተገነቡ የሚገኙ መሰረተ ልማቶችን በመስክ ምልከታ እያካሄዱ ነው፡፡

የሥራ ሃላፊዎቹን  ሉኡካን እየመሩ ያሉት አቶ አዲሱ አረጋ በመዳወለቡ ዩኒቨርሲቲ የጎባ ሪፈራል ሆስፒታል የማስፋፊያ ግንባታ በተመለከቱበት ወቅት እንደገለጹት መንግሥት የህብረተሰቡን መሠረታዊ የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ በቁርጠኝነት እየሰራ ነው፡፡

በሆስፒታሉ እየተካሄደ የሚገኘው ባለ ስምንት ፎቅ ህንፃ የዚሁ ጥረት አካል ሲሉ ጠቅሰዋል፡፡

አቶ አዲሱ የሆስፒታሉ ግንባታ ተቋራጮች ከክፍያ መዘግየት ጋር ተያይዞ ያነሱትን ቅሬታ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው  አካላት ጋር በመወያየት እንደሚፈታ ተናግረዋል፡፡

በመዳወለቡ ዩኒቨርስቲ ጎባ ሪፈራል ሆስፒታል እየተካሄደ ያለው የማስፋፊያ ግንባታ ከአንድ ቢሊዮን 300 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መሆኑ  ተመልክቷል፡፡

በጥላሁን አበበ ጠቅላላ ተቋራጭ ድርጅት የግንባታው ሥራው እየተካሄደ የሚገኘው የሆስፒታሉ የማስፋፊያ ግንባታ ለህሙማን መኝታ የሚውል 470 ክፍሎች እንደሚኖሩት ተገልጿል፡፡

ሆስፒታሉ ለዘመናዊ የህክምና አገልግሎት የሚውሉ ክፍሎች ማካተቱም ተወስቷል፡፡

የሆስፒታሉን ግንባታ በአማካሪነት የሚመራው ፒኤም ቲቲ የተባለ ድርጅት ተወካይ ኢንጅነር ዳዊት ይህይስ  "የሆስፒታሉ የፊዚካል ግንባታ ሂደት 75 ነጥብ 5 በመቶ፣ ፋይናንሺያል አፈፃፀም 55 በመቶ ላይ ይገኛል" ብለዋል፡፡

ከአካባቢው ነዋሪዎች መካከል ሼህ አልይ ከድር በሰጡት አስተያየት የሆስፒታሉ ግንባታ የተሻለ ህክምና በአቅራቢያቸው ለማግኘት ያስችላል ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።

ልኡካኑ ትናንት በባሌ ሮቤና አካባቢው በመንግሥት በጀትና ህብረተሰቡ ተሳትፎ እየተገነቡ የሚገኙ መሠረተ ልማቶችን ተመልክቷል።

በቀጣይ በዞኑ ሲናና ወረዳ በኩታ ገጠም አሰራር  እየለማ የሚገኘውን የእርሻ ማሳ እንደሚመለከቱ የሚጠበቅ መሆኑን ሪፖርተራችን ከሥፍራው ዘግቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም