ቀጥታ፡

ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን አዲስ የቦርድ አባላትን ሹመት አፀደቀ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 15/2013(ኢዜአ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን አዲስ የቦርድ አባላትን ሹመት አፀደቀ። 

ምክር ቤቱ የመገናኛ ብዙኃን ረቂቅ አዋጅና የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ማቋቋሚያን ለማሻሻል የቀረበለትን ረቂቅ አዋጅ ለዝርዝር እይታ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቷል። 

የ6ኛ ዓመት 7ኛ መደበኛ ጉባዔውን ዛሬ ያካሄደው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ሦስት አዲስ የቦርድ አባላትን ሹመት አጽድቋል።

በዚሁ መሰረት ዶክተር አለሙ ስሜ የቦርዱ ሰብሳቢ፣ ዶክተር አረጋዊ በርሄ እና አቶ የሺዋስ አሰፋ አባላት ሆነው የተሾሙ ሲሆን ቃለ መሃላም ፈጽመዋል።

የቦርድ አባላቱ ሹመት በምክር ቤቱ አባላት በሦስት ተቃውሞ በአብላጫ ድምፅ ነው የፀደቀው።

የቦርዱ አባላት የነበሩት ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ፣ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፣ ወይዘሮ የትነበርሽ ንጉሴ፣ ኡስታዝ አቡበከር አህመድ እና ወይዘሮ ካሚያ ጁንዲ ባሉበት ቀጥለዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ቀደም ሲል የነበሩትንና አዲስ ተሿሚዎቹን ጨምሮ በስምንት የቦርድ አባላት የሚመራ ይሆናል።

ምክር ቤቱ በዛሬ ውሎው የመገናኛ ብዙኃን ረቂቅ አዋጅና የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ማቋቋሚያን  ለማሻሻል የቀረበለትን ረቂቅ አዋጅ ለሕግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር እይታ መርቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም