ቀጥታ፡

ባለሃብቶችና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለ"ገበታ ለሀገር" 390 ሚሊዮን ብር ገቢ አደረጉ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 15/2013 ( ኢዜአ) በአዲስ አበባ የሚገኙ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ ባለሀብቶችና የከተማዋ አስተዳደር ለ"ገበታ ለሀገር" 390 ሚሊዮን ብር ገቢ አደረጉ።

ትናንት ምሽት በሸራተን አዲስ በተካሄደ ስነ-ስርዓት ባለሃብቶች ለ"ገበታ ለሀገር" ፕሮጀክቶች ቃል የገቡትን 320 ሚሊዮን ብር፣ የአዲስ አበባ አስተዳደር ደግሞ 70 ሚሊዮን ብር ገቢ አድርገዋል።

ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሜ እና የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ በመርሃ ግብሩ ተገኝተዋል።

ባለሃብቶቹ ገንዘቡን ገቢ ያደረጉበትን ደረሰኝ ለምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስረክበዋል።

ምክትል ከንቲባዋ በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልዕክት በዚህ ትልቅ አገራዊ ፕሮጀክት አሻራቸውን እያሳረፉ ያሉ ባለሀብቶች አገር በማልማት ሃላፊነታቸውን መወጣታቸው ብሔራዊ ኩራት መሆኑን ተናግረዋል።

ለአገራዊው የልማት ፕሮጀክት ቃል ገብተው በተግባር ለተሳተፉ የከተማዋ ባለሃብቶችም ምስጋና ቸረዋል።

በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት እየተሳተፉ ያሉና ቃል የገቡ ድርጅቶችና ባለሀብቶችም በተያዘው ሳምንት መጨረሻ ድረስ  ገንዘቡን ገቢ እንዲያደርጉ ጥሪ አስተላልፈዋል።

ባለሀብቶቹ በበኩላቸው ቀደም ባለው በገበታ ለሸገር ተሳትፏቸውና በተገኘው ውጤት የተሰማቸውን ኩራትና ደስታ ገልፀው ሌሎች ተሳታፊዎችን ለማካተት ተጨማሪ ጊዜ እንዲኖራቸው ጠይቀዋል።

አገራዊ ፕሮጀክቶች እውን እንዲሆኑ የገቢ ማሰባሰቢያዎች ወጥነት ቢኖራቸውና በታክስ መልክ ቢሰበሰቡ መልካም ነው ሲሉም አስተያየታቸውን አክለዋል።

ለ"ገበታ ለሀገር" ፕሮጀክት ቃል ተገብቶ ገቢ ያልሆነ ገንዘብ እስከ መጪው ዓርብ ገቢ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም