ክልሎች ኢንዱስትሪዎችን እንዲያለሙ የተመደበላቸውን 8 ቢሊዮን ብር ፈጥነው እንዲጠቀሙ ተጠየቀ

ባህርዳር፣ ታህሳስ 15/2013 (ኢዜአ) ክልሎች አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን እንዲያለሙ ከዓለም ባንክ የተገኘውን ከ8 ቢሊየን ብር በላይ በጀት ፈጥነው ሊጠቀሙ እንደሚገባ የፌደራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ባለስልጣን አሳሰበ።

ከዓለም ባንክ የተመደበን በጀትን በመጠቀም የኢንዱስትሪ ልማት ትራንስፎርሜሽን ለማሳካት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የመከረ የባለድርሻ አካላት መድረክ ትናንት በባህር ዳር ከተማ ተካሄዷል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ አስፋው አበበ በወቅቱ እንደገለጹት ባለፉት ሦስት ዓመታት በዓለም ባንክ  የበጀት ድጋፍ  ኢንዱስትሪዎችን ለመደገፍ ሲሰራ ቆይቷል።

ድጋፉን መሰረት አድርጎ መንግሥት በመደበው በጀት አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን በማስፋፋት በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሃብቶች የብድር ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን አስታውሰዋል።

"ይሁን እንጂ የክልሎች ሃብትን በአግባቡና ለታለመለት አላማ የማዋል አቅም ውስንነት ጋር ተያይዞ ከ8 ነጥብ 6  ቢሊየን ብር በላይ ገንዘብ ጥቅም ላይ ሳይውል በዓለም ባንክ ተከማችቶ ይገኛል" ብለዋል።

በሚቀጥሉት ስድስት ወራት በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶችንና በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች የተደራጁ ኢንተርፕራይዞችን በመመልመል ገንዘቡን ጥቅም ላይ ማዋል ግድ እንደሚል ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ተከማችቶ የሚገኘውን ገንዘብ በተያዘለት የጊዜ ገደብ መጠቀም ከተቻለ ባንኩ ተጨማሪ 200 ሚሊየን ዶላር ለመመደብ ቃል መግባቱን ዋና ዳይሬክተሩ አመላክተዋል።

በየክልሉ የሚገኙ ወጣቶችንና ባለሃብቶችን በማደራጀትና በበጀት በመደገፍ ወደ ስራ ማስገባት እንደሚገባ አስገንዘበዋል ።

በተለይም እንደ ሰሊጥ፣ ኦፓል፣ ቀርቀሃና እንደየ ክልሎቹ የተፈጥሮ ሀብቶች አቅም ሊለሙ የሚችሉ ጥሬ ዕቃዎችን እሴት ጨምሮ ለውጭ ገበያ በማቅረብ ዕድሉን ሊጠቀሙበት እንደሚገባ አመልክተዋል።

"የዘርፉ ዕድገት ሀገራችን የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆንና በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ውስጥ ለመግባት በምታደርገው እንቅስቃሴ ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚያስችል በመሆኑ ክልሎች በጀቱን በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል ይገባቸዋል" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ዶክተር ዮሃንስ አያሌው በበኩላቸው መንግስት የያዘውን የኢንዱስትሪ ትራንስፎርሜሽን ለማሳካት ባንኩ በአዲስ መልክ የአሰራር ማሻሻያ እያካሄደ መሆኑን አመልክተዋል።

"ማሻሻያው ከዚህ ቀደም በባንኩ ላይ በደንበኞች ይነሳ የነበረውን የተንዛዙና ብልሹ አሰራሮችን በማስቀረት ለተበዳሪዎች ፍትሃዊና ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪውን ለመደገፍ ያስችላል" ብለዋል።

ከዓለም ባንክ የተመደበውን ከ8 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ ገንዘብ ለክልሎች እንደ ህዝብ ብዛታቸው፣ የማስፈጸም አቅማቸውና በብድር አፈጻጸማቸው መሰረት እንደሚደለደል ተናግረዋል።

"በሊዝ ፋይናንስ ወደ ክልሉ የመጣውን ሃብት በአግባቡ ጥቅም ላይ በማያውል አመራርና ተቋም ላይ እርምጃ ይወሰዳል" ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር ናቸው።

"የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት፣ ቴክኒክና ሙያ፣ ንግድና ገበያ ልማትና የሚመለከታቸው ተቋማት የጋራ ኮሚቴ በማቋቋም ከወዲሁ ተጠቃሚዎችን በመለየት፣ ስልጠና በመስጠትና የስራ ቦታ በማዘጋጀት ሃብቱን መጠቀም ይገባል" ብለዋል።

በምክክር መድረኩ የክልል ካቢኔ አካላት፣ አበዳሪ ተቋማት፣ አቅራቢና አምራች ድርጅቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም