ቀጥታ፡

በመተከል ዞን የተፈጠረውን ችግር ከመሰረቱ ለመፍታት መንግስት አስፈላጊው የተቀናጀ ኃይል እንዲሠማራ አድርጓል -ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

ታህሳስ 15/2013 ( ኢዜአ) “በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን ውስጥ ያለውን ችግር ከመሠረቱ ለመፍታት መንግስት አስፈላጊውን የተቀናጀ ኃይል እንዲሠማራ አድርጓል” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፌስቡክ ገጻቸው እንዳስነበቡት “በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ውስጥ በዜጎች ላይ እየተፈጸመ ያለው ጭፍጨፋ እጅግ አሳዛኝ ሆኗል” ብለዋል።

“በወገኖቻችን ላይ በተፈጸመው ኢሰብአዊ ተግባር በእጅጉ አዝኛለሁ” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ ችግሩን በተለያየ መንገድ ለመፍታት የተደረገው ጥረት የሚፈለገውን ውጤት እንዳላመጣ ገልጸዋል።

“የጠላቶቻችን ዓላማ በጁንታው ላይ የሠነዘርነውን ብርቱ ኃይል ለመበተን ነው” በማለት ጠቅሰው፤ ይህ የሚሳካ እንዳልሆነም አስምረውበታል።

“መንግሥት ችግሩን ከመሠረቱ ለመፍታት አስፈላጊውን የተቀናጀ ኃይል እንዲሠማራ አድርጓል” ብለው፤ የሚፈለገውን ውጤት ለማግኘት ሁሉም እንደ ከዚህ ቀደሙ በትኩረትና በኅብረት እንዲሰራ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም