ቀጥታ፡

የተጀመረው ብሔራዊ የምክክር መድረክ ያሉብንን ጊዜያዊ ሕመሞች ለመፈወስ የሚያስችል ነው - የሰላም ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 14 ቀን 2013 (ኢዜአ) “የተጀመረው ብሔራዊ ማህበረሰብ ተኮር የምክክር መድረክ ያሉብንን ጊዜያዊ ሕመሞች ለመፈወስ የሚያስችሉ ናቸው” ሲሉ የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ገለጹ።

በኢትዮጵያ የሚከሰቱ ግጭቶችና ግድያዎች መንስኤያቸው ያሉት ስብራቶች ባለመጠገናቸው እንደሆነም ተናግረዋል።

በሰላም ሚኒስቴር አመቻችነት የተዘጋጀው ብሔራዊ የማህበረሰብ ተኮር ምክክር መድረክ ከሶስት ቀናት በፊት ከትግራይ ክልል በስተቀር በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች መጀመሩ ይታወቃል።

የምክክር መድረኩ መንግስት በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን፣ የሕግ የበላይነት እንዲከበርና ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር የሚሰራቸው ስራዎች አካል ነው።

መድረኩ የአስተሳሰብ ልዕልና ያለው፣ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ስልጡን በሆነ መንገድ በራሱ የሚፈታ እና ቀጣይነት ያለው እድገት የሚያረጋግጥ ማህበረሰባዊ አቅም መፍጠር ዓላማ ያደረገ ነው ተብሏል።

የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ለብሔራዊ የማህበረሰብ ተኮር ምክክር መድረክ ተሳታፊዎች በበይነ መረብ ባስተላለፉት መልዕክት “በኢትዮጵያ አሁን ላይ ልብ የሚሰብሩ፣ ቅስም የሚሰብሩና ለመስማትም ሆነ ለማየት የሚከብዱ ድርጊቶች እየተፈጸሙ ነው” ብለዋል።

ድርጊቶቹ ስብራቶችን ካለመጠገን የመጡና ራሳቸው አባባሽ ምክንያቶች እንዳሏቸው ገልጸዋል።እኔ ያልኩህን ብቻ ተከተል በሚል የራስን አጀንዳ በሰው ላይ ያለ ፍላጎት በጉልበት መጫንም ለሚፈጠሩ ግጭቶችና ግድያዎች ሌላኛው መንስኤ እንደሆነም ጠቅሰው፤ “ይህን ማለፍ የሚቻለው እንደ አገር ያሉብንን ስብራቶች መጠገን ሲቻል ነው” ብለዋል።

‘የማውቅልህ እኔ ብቻ ነኝ’ ከሚል የተሳሳተ እሳቤ ወጥቶ አንዱ የሌላውን ሀሳብ ማዳመጥና ማክበር እንደሚገበውና በጆሮ ሳይሆን በልብ የመደማመጥንና የመከባበር ባህልን ማዳበር ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።

አሁን የተጀመረው ብሔራዊ ማህበረሰብ ተኮር የምክክር መድረክ ያሉብን ጊዜያዊ ሕመሞች ለመፈወስ የሚያስችል መሆኑንም አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ ያሉባትን ብዙ ፈተናዎች ለማለፍ ሁሉም ዜጋ በሃላፊነት ስሜት ሊሰራ እንደሚገባው አመልክተዋል።

መንግስት ሰላም የማምጣት ፖሊሲ ላይ አቅጣጫ ቀይሶ እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ህብረተሰብን አሳታፊ ያደረጉ ውይይቶችን ጨምሮ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ከልሂቃን፣ ፓርቲዎች፣ ምሁራን፣ እምነት ተቋማትና ከሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት ማድረግና የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥን ሰላማዊና የተቀላጠፈ በማድረግ ሰላምን ለማምጣት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

“በብዝሃነት ሁላችንም አንድ አይነት ሀሳብ ይኑረን የሚል ነገር የለም” ያሉት ሚኒስትሯ፤ በተቻለ መጠን የተቀራረበ ሀሳብ መያዝና የተለያዩ ፍላጎቶችን ማስታራቅ የሚያስችል ሁኔታ መፍጠር ለዘላቂ ሰላም ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።

ዘላቂ ሰላምን ለማምጣትና ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር የሕግ የበላይነት ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግና ተናግረዋል።

መንግስት ሕብረተሰብን አሳታፊ ያደረገ ሕግና ስርዓትን የማስከበር ስራ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸው፤ “ከማህበረሰቡ ጋር የሚደረጉ ውይይቶች ይሄን መደላድል ለመፍጠር ወሳኝ ሚና አላቸው” ብለዋል።

የለማች፣የበለጸገችና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የሰፈነባት አገር ለመገንባት ሰላምን በዘላቂነት ማረጋገጥ እንደሚገባና ለዚሁም ሁሉም በቁርጠኝነት ሊሰራ እንደሚገባውም አሳስበዋል።

ብሔራዊ ማህበረሰብ ተኮር የምክክር መድረኩ ከ20 እስከ 25 ሚሊዮን ሰዎች ለማሳተፍ እቅድ መያዙንና ይሄም እውን እንዲሆን የሚመለከታቸው አካላት የበኩላቸውን ሃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

ብሔራዊ የማህበረሰብ ተኮር የምክክር መድረኩ ለሶስት ወራት በቋሚነት የሚዘልቅ ሲሆን በፌደራል ደረጃ የማጠቃለያ መድረክ እንደሚኖር ከሰላም ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም