ቀጥታ፡

በጋራ ድንበር አካባቢ በሱዳን የተደረጉ አዳዲስ ለውጦችና እንቅስቃሴዎች በአስቸኳይ እንዲቆሙና ወደ ቀደመ ቦታቸው እንዲመለሱ ኢትዮጵያ አሳሰበች

ታህሳስ 14 /2013 (ኢዜአ) ከጥቅምት ወር መጨረሻ ጀምሮ በጋራ ድንበር አካባቢ በሱዳን የተደረጉ አዳዲስ ለውጦችና እንቅስቃሴዎች የቀደሙ ስምምነቶችን የሚጥሱ እና መሬት ላይ ያለውን እውነታ የሚለውጡ በመሆናቸው በአስቸኳይ እንዲቆሙና ወደ ቀደመ ቦታቸው እንዲመለሱ ኢትዮጵያ አሳሰበች።

ሁለተኛው የኢትዮጵያ-ሱዳን የድንበር ጉዳዮች የከፍተኛ ደረጃ የፖለቲካ ውይይት በካርቱም ሱዳን ለሁለት ቀናት ታህሳስ 13 እና 14 ቀን 2013 ዓ.ም ተካሂዶ ዛሬ ተጠናቋል።

ሁለቱ ወገኖች በጋራ የድንበር አካባቢ ወቅታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ሃሳቦችን ተለዋውጠዋል።

በዚህም ከጥቅምት ወር መጨረሻ ጀምሮ በጋራ ድንበር አካባቢ በሱዳን የተደረጉ አዳዲስ ለውጦችና እንቅስቃሴዎች የቀደሙ ስምምነቶችን የሚጥሱ እና መሬት ላይ ያለውን እውነታ የሚለውጡ በመሆናቸው በአስቸኳይ እንዲቆሙና ወደ ቀደመ ቦታቸው እንዲመለሱ ኢትዮጵያ አሳስባለች።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ በገበሬዎች እና ባለሃብቶች ንብረት ላይ የደረሰ ከፍተኛ ጉዳት እና የዜጎች መፈናቀል ትኩረት እንደሚያሻው እና በአስቸኳይ መታረም ያለበት መሆኑን ኢትዮጵያ አሳስባለች።

በተጨማሪም የሁለቱ አገሮች የጋራ ድንበርን በተመለከተ ያሉ ማናቸውንም አይነት ልዩነቶች ሁሉንም በሚያስማማ መንገድ በውይይት ስለ መፍታትና የወደፊት አቅጣጫ ምን ይሁን በሚለው ዙሪያ መክረዋል።

በኢትዮጵያ በኩል የድንበሩን ጉዳይ ሰላማዊ በሆነ መልኩ ከቀድሞ ስምምነቶች ጋር በተጣጣመ መንገድ ከድንበሩ ጋር በተያያዘ የተቋቋሙና ስራቸውን ያላጠናቀቁ ልዩ ልዩ ኮሚቴዎችን ስራቸውን እንደገና እንዲጀምሩ በማድረግ፣ መፈታት እንዳለበት ተገልጿል።

ይህም የሁለቱን አገራት ስትራቴጂካዊና ወንድማማቻዊ ግንኙነት እንዲሁም የሁለቱን ህዝቦች ዘላቂ ፍላጎትና ጥቅም የሚያስጠብቅ እንደሚሆን ተገልጿል።

ሁለቱ ወገኖች ቀጣይ ምክክራቸውን ለሁለቱ ወገኖች በሚመች ጊዜ በአዲስ አበባ ላይ ለማካሄድና ለመሪዎቻቸው የዚህኛውን ስብሰባ ሂደትና ውጤት ሪፖርት በማቅረብ በሚሰጣቸው አቅጣጫ መሰረት ምክክራቸውን ለመቀጠል በመስማማት ስብሰባውን አጠናቀዋል።

በቀጣይ ስብሰባ በአካባቢው ያሉ ለውጦችን በመገምገም የድንበር ኮሚቴዎች ስራቸውን የሚቀጥሉበት ሁኔታ ላይ እንደሚመክሩ ይጠበቃል።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በምክትል ጠቅይ ሚኒስትር እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የተመራ ሲሆን ከሱዳን ጠቅላይ ሚኒስተር አብደላ ሃምዶክ እና የሉዓላዊ ምክር ቤት ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ጄኔራል ሞሃመድ ሐምዳን ዳግሎ ጋር ተገናኝተው ውይይት አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም