ቀጥታ፡

የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከአስራኤልና ደቡብ ኮሪያ አምባሳደሮች ጋር ተወያየ

አዲስ አበባ ታህሳስ 14/2013 (ኢዜአ) በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በኢትዮጰያ ከሚገኙ የአስራኤልና የደቡብ ኮሪያ አምባሳደሮች ጋር ተወያዩ።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር ራፋኤል ሞራቭና የደቡብ ኮሪያ አምባሳደር ካንግ ሶኪን ጋር የተወያየ ሲሆን በወቅታዊ የኢትዮጵያ ሁኔታም ለአምባሳደሮች ተገልጾላቸዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከሁለቱ አገራት አቻ ምክር ቤቶች ጋር በትብብር በመስራት ህዝብን በመወከላቸው ህዝባዊ ግንኙነቱን ወደ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እንዲሸጋገር እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ትክክለኛ፣ ታማኒና አሳታፊ አገራዊ ምርጫ እንደምታደርግ ቋሚ ኮሚቴው ያስረዳ ሲሆን አገራቱ ለምርጫው ስኬት ድጋፍና ትብብር እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።

በቅድሚያ የእስራኤሉን አምባሳደር ያነጋገሩት የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ኢትዮጵያና እስራኤል ግንኙነት ተራ ወዳጅነት ሳይሆን የዘመናት ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ትስስር ያዳበሩ መሆኑን አስታውሰዋል።

ሁለቱን ጥንታዊና የቀደምት ስልጣኔ ባለቤት ህዝቦችን በንግድና ኢንቨስትመንት ይበልጥ ማስተሳስር እንደሚገባ በተለይም በዘመናዊ ግብርና ቴክኖሎጂዎች ረገድ ኢትዮጵያ የእስራኤልን ተሞክሮ እንደምትሻ ገልጸዋል።

ቤተ አስራኤላዊያን የኢትዮጵየ አምባሳደሮች እንደሆኑ ገልፀው፣ ይህን አድል አጋጣሚ በመጠቀም የኢትዮ-እስራኤል የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ይበልጥ ለማጠናከር በቋሚ ኮሚቴው ውስጥ አንድ ቡድን ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያና ደቡብ ኮሪያ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ኢትዮጵያ ከደቡብ ኮሪያ ጎን በመቆም ያሳየችውን አጋርነት ተከትሎ የሁለቱ አገራት ህዝቦች ግንኙነት በደም መስዋትንት ላይ የተሰመረተ ሁለንተናዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መመስረቱን ገልጸዋል።

ደቡብ ኮሪያ በዕድገት ማማ ላይ የወጣችበትን የኢኮኖሚ ሞዴል እንደምታደንቅ ገልጸው፤ በተለይም በኤሌክትሮኒክስ ቴክኖሎጂና በትምህርት ዘርፍ ያላትን ዕምቅ አቅም በኢትዮጵያ እንድታስፋፋ ጠይቀዋል።

ኮሪያ የኢትዮጵያን የልማት አጋርነት አድንቀው፣ ከህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ ማጠናከር ባሻገር በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በቱሪዝም፣ በደንና አየር ንብረት ለውጥ፣ በቴክኖሎጂ መስኮች ትብብራቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው ተናጋግረዋል።

የሁለቱ አገራት አምባሳደሮች ኢትዮጵያ ከአገራቱ ጋር ያላት ታሪካዊ ወዳጅነትና የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ባለፈ ለአፍሪካ ህብረት መቀመጫ በመሆኗ ከአፍሪካ ጋር ለሚኖራችው ግንኙነትም ስትራቴጂክ አጋር መሆኗን ገልጸዋል።

አምባሳደር ራፋኤል ሞራቭ በበኩላቸው እስራኤል ምጣኔ ሀብታዊ፣ በማህበራዊና በፖለቲካዊ ዲፕሎማሲዊ ግንኙኙነታቸው ላይ ይበልጥ ማጠናከር እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

የደቡብ ኮሪያው አምባሳደር ካንግ ሶኪ በበኩላቸው ህዝብ ህዝብ ግንኙነት እንዲጠናከር፣ የንግድ ልውውጣቸው እንዲሰፋ፣ የኮሪያ ባለሀብትች በኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸው፣ በኢትዮጰያ በኩል ለኢንቨስትምነት አስቻይ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩም ጠይቀዋል።

የሁለቱ አገራት ምክር ቤቶች የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ እንደሚሰሩ አረጋገጠዋል።

ኢትዮጰያ የ10 ዓመታት የልማት እቅድ አውጥታ እየሰራች መሆኗን አብራርተዋል።

በትግራይ ክልል መንግስት የህወሃት ቡድንን የሽብር እንቅስቃሴ ቢታገስም በመጨረሻም ቀይ መስመር በማለፍ በመከላከያ  ሰራዊት ላይ ጥቃት በመፈጸም አገርን ህልውላና አደጋ ላይ በመጣሉ መንግስት ወደ ሕግ ማስከበር ተገዶ መግባቱን አስረድተዋል።

በዚህም አሁን ላይ የሕግ ማስከበር ስራው ተጠናቆ ጊዜያዊ አስተዳድር መዋቀሩን፣ የተጎዱ መሰረት ልማቶች የመጠገን ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

አምባሳደሮቹም ማንም አገር ሉዓላዊነትን የሚፈታተን ሁኔታዎች ሲከሰቱ መደራደር እንደማይገባ ገልጸው፣ የህግ ማስከበር ስራውንም እንደሚደግፉ ገልጸዋል።

የህግ ማስከበር ስራውን በትኩረት ሲከታተሉ እንደነበር ገልጸው፣ በክልሉ ንጹሃን እንዳይጎዱ ተገቢው ሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ መሰራት ይገባል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት አገሮቻቸው ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አምባሳደሮቹ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም