ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የተቀናጀ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ባለመኖሩ "አንዱ የገነባውን ሌላው እያፈረሰና ከፍተኛ ወጪ እያስከተለ" ቀጥሏል

አዲስ አበባ ታህሳስ 14/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የተቀናጀ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ባለመኖሩ "አንዱ የገነባውን ሌላው እያፈረሰና ከፍተኛ ወጪ እያስከተለ" መቀጠሉን የፌዴራል የተቀናጀ የመሰረተ ልማት ማስተባበሪያ ኤጀንሲ እስታወቀ።

በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ አዲስ የኤሌክትሪክ መስመር ለመዘርጋት ጉዳት የሚደርስባቸውን መሰረተ ልማቶች መልሶ ለመገንባት 20 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ብለዋል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ ልማት ኮንስትራክሽንና የትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አማካኝነት ቅንጅታዊ አሰራሩን አስመልክቶ ውይይት ተደርጓል።

የፌዴራል የተቀናጀ መሰረተ ልማት ማስተባበሪያ ዋና ዳይሬክተር አቶ አልማው መንግስቴ እስካሁን ያለውን ቅንጅታዊ አስራር ሪፖርት አቅርበዋል።

በሪፖርታቸውም ቅንጅታዊ አሰራሩን ያስተባብራል ተብሎ በ2006 ዓ.ም የተቋቋመው ኤጀንሲ ወደ ስራ ለመግባት የሞከረው በ2009 ዓ.ም ነው ብለዋል።

ኤጀንሲው በ2011 ዓ.ም በትክክል ስራ መጀመሩን ጠቅሰው በተደረገው ክትትል የቅንጅት ማነሱ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም መሰረተ ልማት በሚዘረጉ ተቋማት መካከል የቅንጅት ባህል አለመኖር፣ ተጠያቂነት አለመኖርና መንግስትም ለዚህ ጉዳይ ትኩርት አልሰጠም ብለዋል።

ይህ መሆኑ ደግሞ በአጠቃላይ የአገሪቷ ፕሮጀክቶች የጊዜ መውሰድ፣ ከፍተኛ ወጭና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እያስከተሉ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም የፕሮጀክቶች ካሳ ክፊያ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ኪሳራ እያጋጠመ መሆኑን ገልጸው በአንድ ቀበሌ ለአንድ ዛፍ እስከ 25 ሺህ ብር እየተከፈለ መሆኑን አንስተዋል።

በመሰረተ ልማት ዝርጋታ ላይ የተሰማሩ የፌዴራል ተቋማትም ችግሩ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እየደረሰ መሆኑን ጠቅሰዋል።

እነዚሁ ተቋማት አስፈላጊ መረጃ እንኳን የሚለዋወጡበት አሰራር ባለመኖሩ አንዱ የገነባውን ሌላው እያፈረሰ ይገኛል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሽፈራው ተሊላና የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ሀብታሙ ተገኝ የችግሩን አሳሰቢነት አብራርተዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ አዲስ የኤሌክትሪክ መስመር ለመዘርጋት ጉዳት የሚደርስባቸውን መሰረተ ልማቶች መልሶ ለመገንባት 20 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ብለዋል።

የኢትዮጵ መንገዶች ባለስልጣንም በሂደት ላይ ያሉት 300 ፕሮጀክቶች በተያዘው ጊዜና ገንዘብ ለመጨረስ ያስቸግራል ብለዋል።

በተለይ ደግሞ ከካሳ ክፊያ ጋር በተያያዘ ባለስልጣኑ አምና 4 ቢሊዬን ያወጣ ሲሆን ዘንድሮ ምናልባት እስከ 8 ቢሊዬን ሊደርስ እንደሚችል ተገምቷል ብለዋል ኢንጅነር ሀብታሙ።

የቋሙ ኮሚቴ አባላቱም በመሰክ ምልከታ የቅንጅት ችግሩ አሳሳቢ መሆኑን መመልከታቸውንም ይገልጻሉ።

በተለይ በአማራ ክልል ሁለት ቦታዎች ላይ የኤሌክትሪክ ፖል ባለመነሳቱ ምክንያት የመንገድ ግንባታ ተጓቷል ብለዋል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴም የህዝቡን የመሰረተ ልማት ለማሟላት በብድርና በእርዳታ ጭምር የሚሙ በቢሊዬን የሚቆጠር ብር እየባከነ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ ደግሞ በከተሞች አካባቢ ችግሩ ከፍተኛ የኃብት ብክነት እያስከተለ መሆኑን ነው የገለጹት።

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትሯ ኢንጀነር አይሻ መሓመድ እና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ እንደ አገር ችግሩ አሳሳቢ በመሆኑ ወጥ አሰራር ሊዘረጋ ይገባል ብለዋል።

በቀጣይ የተሻለ የአሰራርና አመራር ስርዓት ካልተዘረጋለት ችግሩ የበለጠ ዋጋ እያስከፈለ መሄዱ አይቀርም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም