ቀጥታ፡

ፖሊስ ባደረገው ፍተሻ በሚሊዮን የሚቆጠር ሃሰተኛ እና በህገ ወጥነት የተገኘ ገንዘብ መያዙን አስታወቀ

አዲስ አበባ ታህሳስ 14/2013 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የከተማዋን ደህንነት ለማስጠበቅ እያካሔደ ባለው ፍተሻ እስካሁን ከ4 ሚሊዮን በላይ የኢትጵያ ብር ና ከ430 ሺህ በላይ የተለያዩ አገራት ሀሰተኛ የገንዘብ ኖቶችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገለፀ።

የኮሚሽኑ የህዝብ ግኑኙነት ዳይሬክተር ኮማንድር ፋሲካ ፈንታ ለኢዜአ እንደገለጹት ፖሊስ 4 ሚሊዮን 300 ሺህ የኢትዮጵያ ብር፣ 248 ሺህ 941 የአሜሪካ ዶላር፣ 3 ሺህ 172 ዩሮ እና ከ192 ሺህ በላይ በህገ ወጥ የተገኙ የገንዘብ ኖቶችን በቁጥጥር ስር አውሏል።

በተጨማሪም 178 ሺህ 265 ብር፤ 181 ሺህ 9 መቶ የአሜሪካ ዶላር እና 200 ዩሮ ሃስተኛ ኖቶችን በቁጥጥር ስር በማዋል በተጠርጣሪዎች ላይ ምርመራ እየተካሔደ መሆኑን ነው የገለፁት።

እንደ ኮማንደር ፋሲካ ገለጻ በአንድ ወር ውስጥ የሕወሃት የጥፋት ቡድን በአገር ኢኮኖሚና ጸጥታ ላይ አደጋ ለመደቀን በርካታ ጥረቶችን አድርጓል።

ቡድኑ በርካታ የጦር መሰሪያዎች፣ የውጭና የአገር ውስጥ ሃስተኛና ህገ-ወጥ የገንዘብ ኖቶችን በማዘጋጀት ሲንቀሳቀሱ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስረድተዋል።

ባለፋት አንድ ወራት ፖሊስ በከተማዋ ባደረገው ከፍተኛ ቁጥጥርና ፍተሻ እነዚህ ሀሰተኛና ህገ-ወጥ የብር ኖቶች ሊያዙ እንደቻሉም ነው የጠቆሙት።

በቀጣይም በዚህ ህገ ወጥ ተግባር የተሰማሩትን ቡድኖች  በጸጥታ ኃይሉና በህብረተሰቡ ትብብር በቁጥጥር ስር የማዋል ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ህብረተሰቡ በዚህ ህገ ወጥ ተግባር ላይ የተሰማሩ አካላትን የማጋለጥና ለፖሊስ ጥቆማ መስጠቱን እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

በግብይት ወቅትም ሃስተኛ የብር ኖቶችን በጥንቃቄ በመለየት ሊያከናውን እንደሚገባ ነው ኮማንደር ፋሲካ ያሳሰቡት።    

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም