ቀጥታ፡

በፓርኮችና በቱሪዝም መዳረሻዎች ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለማቃለል የተቀናጀ አሰራር እንደሚያስፈልግ ተገለጸ

አዲስ አበባ ታህሳስ 14/2020 (ኢዜአ) በፓርኮች እና በቱሪስት መስህቦች አካባቢ የሚታዩ የተለያዩ ችግሮችን ለማቃለል የተቋማት የተቀናጀ አሰራር አስፈላጊ መሆኑን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገለጸ።

በምክር ቤቱ የግብርና አርብቶ አደርና አካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽንና በስሩ ያሉ ተጠሪ ተቋማትን የሩብ አመት እንቅስቃሴ ገምግሟል፡፡

የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ አበባየ ገዛህኝ የተቋማቱን የሩብ ኣመት አፈጻጸም ግምገማ ባቀረቡበበት ወቅት "በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ፓርኮችና የቱሪስት ተቋማት የተለያዩ ችግሮች ተጋርጦባቸው" ብለዋል፡፡

በአዋሽ ፣ነጭ ሳር፣ ባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ ፣ አብያታና ሻላ ሀይቆች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ከአካባቢው የመንግስት አካላት ጋር በመቀናጀት መፍታት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ከፓርኮቹና የቱሪስት መዳረሻዎቹ ሀገሪቱ ከፍተኛ ገቢ ማግኘት የምትችል ቢሆንም በአያያዝ እና ባልተቀናጀ የኢንቨስትመንት አሰራር ለጉዳት በመዳረግ ለመጥፋት መቃረባቸውን ቋሚ ኮሚቴው መመልከቱን አስታውቀዋል፡፡

የህብረተሰቡን ችግሮች የሚፈቱ የተለያዩ የምርምር ስራዎችን በማከናወንና የአካባቢ ጥበቃ ስራን በንቅናቄ በመምራት በኩል ኮሚሽኑ ያከናወናቸው ተግባራት በጥንካሬ የሚወሰዱ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

ኮሚሽኑ የተለዩትን ችግሮች ለመፍታት የሚያስችሉ አዋጆች፣ ደንቦችና መመሪያዎች ቢዘጋጁም በሚመለከተው አካል በማስጸደቅ ወደ ተግባር በማስገባት ረገድ ውስንነቶች ስላሉበት ጠንክሮ መስራት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

የአካባቢ ዴንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ በቋሚ ኮሚቴው የተሰጠው ግብረ መልስ ጉድለታቸውን በመሙላት የተሻለ ስራ ለመስራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

ለዚህ ይረዳው ዘንድ ኮሚሽኑ በስሩ ከሚገኙ ሶስት ተጠሪ ተቋማት ጋር የተቀናጀ አሰራር ዘርግቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተለይም በፓርኮችና በቱሪስት መዳረሻዎች እንዲሁም በምርምር ይዞታዎች ላይ የሚፈጸሙ ህገወጥ ተግባራትን ለመከላከል ከክልልና ከፌደራል ተቋማት ጋር በመናበብ እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ኮሚሽኑ በፓርኮች አካባቢ የሚታዩ ህገ ወጥ ሰፈራዎችንና የማዕድን ማውጣት ስራዎችን ለማስቀረት የሚረዱ ህጎችና መመሪዎችን አውጥቶ ለሚመለከተው አካል ማቅረቡን አስታውቀዋል፡፡

ህጎቹና መመሪዎች ጸድቀው ተግባራዊ እንዲሆኑ ቋሚ ኮሚቴው ክትትል እንዲደርግም ጠይቀዋል፡፡

በኮሚሽኑ ስር በተጠሪነት የሚገኙት ተቋማት የኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢኒስቲቲዩት ፣ የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣንና የኢትዮጵያ አካባቢና ደን ምርምር ኢኒስቲቲዩት ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም