ቀጥታ፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ይገባል

ታህሳስ 14/2013 (ኢዜአ) የፖለቲካ ፓርቲዎች የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር እንደሚገባቸው ተጠቆመ።

የሲቪክ ማህበራትም ሴቶችን በማብቃት የፖለቲካዊ ተሳትፏቸውን እንዲያሳድጉ የማድረግ ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው ተገልጿል።

በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሴቶች ጉዳይ የጋራ ትብብር አማካኝነት "የሴቶችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ በምን አይነት መልኩ ማሳደግ ይገባል" በሚል የቨርቿል ስልጠና እየተሰጠ ነው።

በስልጠናውም ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ሲቪክ ማህበራት የተውጣጡ አካላት በመሳተፍ ላይ ናቸው።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የሴቶችና ህጻናት መብት ከፍተኛ አማካሪ ወይዘሮ ዜናየ ታደሰ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሴቶችን በምርጫ ታዛቢነት፣ በመራጭነትና ተመራጭነት ሂደት ንቁ ተሳትፊ እንዲሆኑ መስራት አለባቸው።

የሲቪክ ማህበራት ሴቶችን በትምህርትና ስልጠና በማብቃት ከገጠር እስከ ከተማ በሚከናወኑ ፖለቲካዊ ሁነቶች ላይ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ የማድረግ ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የሴቶችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ ወደ ፊት ለማምጣት የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በመለየት የህግ፣ የፖሊሲና ስትራቴጂ ማእቀፎቻቸውን አካታች ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም አንስተዋል።

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ቃል-አቀባይ አቶ ሙላቱ ገመቹ "በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርዓት ስር አለመያዙና በተለያዩ የስራ ጫናዎች ምክንያት የሴቶችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ ማሳደግ አልተቻለም" ብለዋል።

ይህን ችግር ለመፍታት የሲቪክ ማህበራትና መንግስት የሴቶችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ ማሳደግ የሚያስችሉ ተከታታይ የስልጠና እና የልምድ ልውውጥ ድጋፍ መስጠት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ሴቶችና ወጣቶችን ማማከር የተሰኘ ግብረ-ሰናይ ድርጅት ስራ አስኪያጅ አቶ አማረ ፈለቀ እንደሚሉት፤ በአገሪቱ ያሉ ሴቶችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለማሳደግ ሁኔታዎችን መሰረት ያደረገ የግንዛቤ ማሳደጊያ ትምህርት መስጠት ይገባል።

"የሴቶችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለማሳደግ የሚያስችሉ በቴሌቪዥን፣ ሬዲዮና ጋዜጣ የተደገፉ ፕሮግራሞችን በስፋት በማሰራጨት የመምረጥና መመረጥ መብታቸውን ማረጋገጥ እንዲችሉ መስራት ያስፈልጋል" ብለዋል።

ስልጠናው የሴቶችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለማሳደግ የሚረዳና ትምህርት ሰጪ እንደሆነ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም