ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀልና የአዲስ አበባ አስተዳደር በህግ ማስከበሩ ዘመቻ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ አደረጉ

ጎንደር/ ባህርዳር ታህሳስ 14/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበርና የአዲስ አበባ አስተዳደር ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የምግብ እህል፣ መድሃኒትና ሌሎች ቁሳቁሶቸ ድጋፍ አደረጉ።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የጎንደር ቅርንጫፍ አስተባባሪ  አቶ አታለል ታረቀኝ  ለኢዜአ እንደተናገሩት በዳንሻ አካባቢ በመጠለያ ለሚገኙ 200 ሴቶችና ህጻናት የአልሚ ምግብ ድጋፍ ተደርጓል፡፡

በአብደራፊ አካባቢ ለሚገኙ 400 አባወራ ተፈናቃዮች ደግሞ ከ600 በላይ ብርድ ልብሶች ጨምሮ የውሃ መጠጫና መመገቢያ ቁሳቁሶች መከፋፈሉን አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም ተፈናቃዮቹ ለመጠለያ የሚያውሉት ፕላስቲኮች በአባወራ  ደረጃ  በማሰራጨት  የገጠማቸውን የመጠለያ ችግር  ለማቃለል ጥረት  መደረጉን  አመልክተዋል፡፡

እንዲሁም ግምታቸው ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ  የሚያወጡ የህክምና  መድሃኒ ቶችን  ደግሞ ለሁመራ ሆስፒታል፣ ዳንሻና ቱርካን ጤና ጣቢያዎች ማህበሩ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም ማህበሩ ዛሬ በደባርቅ ከተማ በጊዚያዊ  መጠለያ ለሚገኙ ከ800  በላይ  ተፈናቃይ የህብረተሰብ ክፍሎች  ብርድ ልብሶች፣ የግል ንጽህና መጠበቂያ፣ የውሃ መቅጃ ጄሪካኖችና የመመገቢያ ቁሳቁሶች ለማሰራጨት የማጓጓዝ ስራ መጀመሩንም አስተባባሪው ጠቁመዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በህግ ማስከበር ሂደቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች የሚውል ሦስት ሺህ ኩንታል የምግብ እህል ድጋፍ  ለአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳደር ዶክተር ፈንታ ማንደፍሮ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ አስረክቧል።

ድጋፉን ያስረከቡት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእሳትና አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር አቶ ሠለሞን ፍሰሃ ለተጎጂዎች የተሰጠው ድጋፍ የበቆሎ፣ ጤፍና  ስንዴ እህል መሆኑን ተናግረዋል።

የምግብ እህሉ በከተማ አስተዳደሩ ከሚገኙ ባለሃብቶች፣ ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎችና የከተማ አስተዳደሩ የተገኘ ድጋፍ መሆኑን ገልጸዋል።

ድጋፉ ጁንታው ህወሓትን ሥርዓት ለማሲያዝ በተካሄደው ህግ የማስከበር ዘመቻ ከቀያቸው ለተፈናቀሉና ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች የሚውል  መሆኑን ያመለከቱት  አቶ ሠለሞን  ተቋቁመው ወደ መደበኛ ኑሯቸው እስኪመለሱ ድረስ የከተማ አስተዳደሩ እገዛ እንደሚቀጥልም  አስታውቀዋል።

የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ፈንታ ማንደፍሮ በበኩላቸው በተለይም በማይካድራ ከተማ አካባቢ በህወሓት ጨካኝ ቡድን ምክንያት የደረሰው ዘግናኝ ግፍ ቁሳዊ ብቻ ሳይሆን ስነ-ልቦናዊ ድጋፍ ጭምር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ድጋፍ የመጀመሪያው እንዳልሆነ  ገልጸው፤ ችግሩን ተረድቶ እያደረገ ላለው ድጋፍም በክልሉ መንግስትና ህዝብ ስም ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም