በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃ የእስራኤል ባለሀብቶችን ቀልብ ስቧል - አምባሳደር ራፋኤል ሞራቭ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃ የእስራኤል ባለሀብቶችን ቀልብ ስቧል - አምባሳደር ራፋኤል ሞራቭ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 14/2013 ( ኢዜአ) በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃ የእስራኤል ባለሀብቶችን ቀልብ መሳቡን በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር ራፋኤል ሞራቭ ገለጹ።
እስራኤል በኢትዮጵያ ለተጀመረው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ስራ ድጋፍ እንደምታደርግም አመልክተዋል።
በእስራኤል የኢትዮጵያ ኤምባሲና የእስራኤል አፍሪካ የንግድ ምክር ቤት ጋር በመተባበር በኢንቨስትመንት ጉዳይ ላይ ያዘጋጁት የበይነ መረብ የውይይት መድረክ ትናንት ተካሄዷል።
በውይይቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ጽዮን ተክሉ፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁንና በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር ራፋኤል ሞራቭ ተሳትፈዋል።
በእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካና ላቲን አሜሪካ ኢኮኖሚ ጉዳዮች ዳይሬክተር ሚስ ሚሃል ጉር-አርዬህ፣ የእስራኤል ባለሃብቶች የንግድ ማህበረሰብ አባላት እንዲሁም በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ እና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የተሰማሩ ኩባንያዎች ተወካዮች መሳተፋቸው ነው የተገለጸው።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ጽዮን ተክሉ መንግስት ነጻነትን እና ብልጽግናን በኢትዮጵያ ለማስፈን የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎችን እየወሰደ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ከማሻሻያ እርምጃዎች ውስጥ በግሉ ዘርፍ የሚመራ ሁሉን አቀፍና ዘላቂ ልማት መፍጠር አንዱ ነው ብለዋል።
በአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ እንዲሁም የቴሌኮምና የሎጅስቲክ ዘርፎች ለግሉ ባለሀብት ክፍት መደረጋቸው መንግስት ለኢኮኖሚ ማሻሻያው ያለውን ቁርጠኝነት ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።
መንግስት በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ላላቸው የእስራኤል ባለሀብቶች የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አመልክተዋል።
በእስራኤል የኢትዮጵያ አምባሳደር ረታ ዓለሙ ኢትዮጵያ እና እስራኤል ጠንካራ ታሪካዊ እና መንፈሳዊ ትስስር ያላቸው አገራት ናቸው ብለዋል።
በከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ደረጃ የተደረጉት ጉብኝቶች እና የተደረሱት የሁለትዮሽ ስምምነቶች በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን መግባባት እና ወዳጅነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ከዓመት በፊት በእስራኤል ባደረጉት ጉብኝት ሁለቱ ሀገራት ኢኮኖሚያዊ ግንኙነታቸውን ለማሳደግና ስትራቴጂክ ትስስር ለመፍጠር በተደረሰው መግባባት መሰረት የዚህ አይነት ምክክሮች የሚኖራቸው ሚና ወሳኝ ነው ብለዋል።
ሁለቱ ሀገራት ከታሪካዊ ግንኙነታቸው አንጻር የኢኮኖሚ ትብብራቸውን ለማስፋት መስራት እንደሚጠበቅባቸውና የኢትዮጵያ መንግስት በጋራ ተጠቃሚ በሚያደርጉ ዘርፎች ትስስሩን የበለጠ ለማጠናከር ቁርጠኛና ዝግጁ መሆኑን ነው አምባሳደር ረታ ያስረዱት።
በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር ራፋኤል ሞራቭ ኢትዮጵያ እስራኤል ካላቸው ወዳጅነት እና የጠበቀ ግንኙነት አንጻር ያላቸው የኢኮኖሚ ትብብር በሚፈለገው መጠን አለማደጉን ገልጸዋል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት ኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ሁኔታውን ለውጭ ባለሀብቶች የበለጠ የተመቻቸ ለማድረግ ማሻሻያ ስታደርግ መቆየቷን አውስተዋል።
ኢትዮጵያ እምቅ የኢንቨስትመንት ዕድሎች አላት ያሉት አምባሳደሩ በኢትዮጵያ የተካሄደው የኢኮኖሚ ሪፎርም የእስራኤል ኢንቨስተሮችን ቀልብ የሳበ መሆኑን ተናግረዋል።
እስራኤል በኢትዮጵያ ለተጀመረው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ስራ ድጋፍ እንደምታደርግም አመልክተዋል።
በውይይቱ ላይ የተሳተፉት ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ኢትዮጵያ ያሏትን የኢንቨስትመንት እድሎች አማራጮች አስመልክቶ ለእስራኤል ባለሀብቶች ገለጻ አድርገዋል።
በተለያዩ መስኮች በኢትዮጵያ የተሰማሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ተሞክሯቸውን አቅርበዋል።
የእስራኤል አፍሪካ ንግድ ምክር ቤት ተወካዮችም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በንግድ እና ኢንቨስትመንት ፍሰት የፈጠረውን ጫናና ወደ ፊት እንቅስቃሴውን ለማበረታታት በጋራ መከናወን ስለሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ መስጠታቸውን በእስራኤል የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ኢትዮጵያና እስራኤል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ 1963 ሲሆን ሁለቱ አገራት በየአገራቱ ኤምባሲያቸውን በመክፈት የዲፕሎማሲ ግንኙነታቸውን እያደረጉ ይገኛል።
በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርት፣ ባህልና ቱሪዝም ጥሩ ትብብር አላቸው።
የእስራኤል የኢሚግሬሽንና የውህደት ሚኒስትር ሚስ ኒና ታማኖ-ሻታ በሕዳር ወር እንዲሁም የእስራኤል የደህንነት ምክትል ሚንስትር ጋዲ የቫርካን በጥቅምት ወር የአገራቱን ሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከር አላማ ያደረገ ጉብኝት በኢትዮጵያ ማድረጋቸው ይታወሳል።
ኢትዮጵያና እስራኤል ያላቸው የንግድ ልውውጥ 200 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ኢትዮጵያ ወደ እስራኤል ቡና፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ቅመማ ቅመም በዋናነት ስትልክ ማሽኖች፣ የኤሌክትሮኒክስ ምርቶች፣ የኬሚካል ውጤቶችና የሕክምና መሳሪያዎችን ታስገባለች።