ሰራዊቱ የተበታተነውን የጁንታው ታጣቂ ሃይል እየለቀመ በመያዝ ላይ ነው...ሜጀር ጄኔራል እንዳልካቸው ወልደኪዳን - ኢዜአ አማርኛ
ሰራዊቱ የተበታተነውን የጁንታው ታጣቂ ሃይል እየለቀመ በመያዝ ላይ ነው...ሜጀር ጄኔራል እንዳልካቸው ወልደኪዳን
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 14/2013 ( ኢዜአ) የአገር መከላከያ ሰራዊት የተበታተነውን የጁንታው ታጣቂ ሃይል እየለቀመ በመያዝ ላይ መሆኑን የሽሬና አካባቢው የሎጂስቲክስ አስተባባሪ ሜጀር ጄኔራል እንዳልካቸው ወልደኪዳን ገለጹ።
በህወሃት ጁንታ ላይ መንግስት ሲያከናውን የነበረውን የህግ ማስከበር ዘመቻ በሶስት ሳምንት አጠናቆ ወንጀለኞችን በማደን ላይ ይገኛል።
ወንጀለኞችን ከማደን በተጓዳኝ የመልሶ ግንባታና ሰብአዊ ድጋፍም በተጠናከረ መልኩ ቀጥሏል።
በዚህ ሂደት ጁንታው አስታጥቋቸው የነበሩና አሁን ላይ ራሳቸውን ለመደበቅ ተበታትነው የሚገኙትን አባላቱን ለቅሞ የመያዝ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ሜጀር ጄኔራል እንዳልካቸው ለኢዜአ ገልጸዋል።
በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም ለመፍጠር ወንጀለኞችን አድኖ በመያዝ ለህግ ለማቅረብ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የጁንታው ታጣቂ ኃይል ሙሉ ለሙሉ በመደምሰሱ በየትኛውም አካባቢ የሚቆጣጠረውና የሚያስተዳድረው አካባቢ እንደሌለም አረጋግጠዋል።
የአስቸኳይ ጊዜ ሰብዓዊ እርዳታ ያለ ምንም የፀጥታ ስጋት ለህዝቡ እንዲደርስ ሰራዊቱ የድርሻውን እየተወጣ መሆኑንም ሜጀር ጄኔራል እንዳልካቸው ገልጸዋል።
የኢዜአ ሪፖርተር በተንቀሳቀሰባቸው ሽሬና አካባቢው እንዳረጋገጠው ሰብዓዊ እርዳታ እየደረሰ ሲሆን ማህበረሰቡም ወደ መደበኛ እንቅስቃሴው ተመልሷል።