አዲሱ የደሴ ከተማ አመራር የመልካም አስተዳደርና የልማት ችግሮችን ለመፍታት ትኩረት ሊሰጥ ይገባል.... የከተማዋ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
አዲሱ የደሴ ከተማ አመራር የመልካም አስተዳደርና የልማት ችግሮችን ለመፍታት ትኩረት ሊሰጥ ይገባል.... የከተማዋ ነዋሪዎች
ደሴ ሀምሌ 13/2010 በአዲስ መልክ የተዋቀረው የደሴ ከተማ አስተዳደር አመራር የከተማዋን የመልካም አስተዳደርና የልማት ችግሮች ለመፍታት ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ ኢዜአ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት አምስተኛ ዓመት 20ኛ መደበኛ ጉባኤ ትናንት ማምሻውን የሁለት ከንቲባዎችንና የሁለት ዳኞችን ሹመት በማጽደቅ ተጠናቋል፡፡ ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል በደሴ ሆጤ ክፍለ ከተማ የሚኖሩት አቶ ጋሻው ደምሴ እንዳሉት አመራሩ ብቃትን ሳይሆን የግል ቅርበትን መሰረት ያደረገ የሹመት አሰጣጥን ማስወገድ ከተቻለ ህዝባዊ አገልጋይነት ይረጋገጣል። እስካሁን አመራሩ ላይ በሚስተዋሉ አድሏዊ አሰራር ፣ ሙስናና የብቃት ማነስ ችግሮች ሕብረተሰቡን ሲያማርሩ መቆየታቸውን ጠቁመው አዲሱ አመራር ችግሮችን ለይቶ መፍታት በሚያስችል አግባብ መንቀሳቀስ እንዳለበት አመልክተዋል። የከተማዋ ነዋሪዎች በተለይም ወጣቱ ትውልድ አዲሱን አመራር በመደገፍ ለለውጡ ቀጣይነት እንዲሰራ የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡም አቶ ጋሻው ተናገረዋል። የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ ፀሐይነሽ ዓለሙ በበኩላቸው አመራሩን ማቀያየር ብቻ ለውጥ ይመጣል ብለው እንደማያምኑ ጠቁመው፣ አሮጌ አሰራርን በመቀየር በደንበኛው ላይ የሚደርሱ መጉላላትን ማስቀረትም ሌላው ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል። "አዲሱ አመራር በሀሰት ሪፖርት የተዛባ ውሳኔ ላይ እንዳይደርስ ታች ካለው የሕብረተሰብ ክፍል ጋር ቀጥተኛ ውይይት በማካሄድ ህዝቡን የመፍትሄው አካል ማድረግ ይኖርበታል" ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡ ወይዘሮ ፀሐይነሽ እንዳሉት በግል ባለሃብቱ በሚደረገው ውስን ጥረት ብቻ ከተማዋን ከሌሎች ከተሞች ጋር ተወዳዳሪና ለኑሮ ምቹ ማድረግ አይቻልም። "በመሆኑም አዲሱ አመራር የአካባቢ ተወላጆችንና ሌሎች ባለሀብቶችን በመሳብ የህዝቡን ዘርፈ ብዙ ጥያቄዎች ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይጠበቅበታል" ብለዋል።፡ የደሴ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ተስፋዬ ጫኔ ለኢዜአ እንደገለፁት ባለፉት ዓመታት በከተማዋ የተከናወኑ የልማት ሥራዎች ቢኖሩም ከህዝቡ የመልማት ፍላጎት አንጻር ሲታይ ውስንነቶች ነበሩ። "በከተማዋ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን ለመፍታት የነበረውን የሃብት ማመንጨት ችግር በመቅረፍ የህብረተሰቡን ፍላጎት ማርካት የአዲሱ አመራር የትኩረት አቅጣጫ ይሆናል" ሲሉም ገልጸዋል። በእዚህም የመሰረተ ልማት ስራዎችን ለማሟላት፣ ህገ ወጥ ንግድን ለማስቆም፣ የወጣቱን ጥያቄ ለመፍታትና የከተማዋን ማስተር ፕላን ታሳቢ ያደረገ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎችን የማስፋፋት ሥራ እንደሚከናወን አስታውቀዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ህዝቡ እያሳየ ያለውን የለውጥ እንቅስቃሴ መርቶ ወደ ላቀ ደረጃ የሚያደርስ ወጣት ምሁራንን በሹመት ወደ ላይ ለማውጣት መሰራቱን የገለጹት ደግሞ የከተማዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ - ጉባኤ አቶ ሀሰን ሙህዬ ናቸው። ይህም ሕብረተሰቡ እስከዛሬ ሲያነሳቸው የነበሩ ቅሬታዎችና የልማት ጥያቄዎች በአግባቡ ተረድቶ በተጀመረው የ2011 አዲስ በጀት ዓመት ተገቢ ምላሽ ለማስጠት የተሻለ ዕድል እንደሚሰጥ አመልክተዋል። የከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት አራተኛ ዙር አምስተኛ ዓመት 20ኛ መደበኛ ጉባኤውን ትናንት ማምሻውን ሲያጠናቅቅ ለደሴ ከተማ ዶክተር መሰለ መኮንን በተቀዳሚ ምክትል ከንቲባነት እንዲሁም አቶ ተስፋዬ ጫኔን በምክትል ከንቲባነት መሾሙ ታውቋል። በተጨማሪም ወይዘሪት ብሩክታይት ወንድሙንና አቶ ልኡልፀጋ ልሳነ ወርቅን በከተማ ነክ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኛ አድርጎ ሾሟል። ምክር ቤቱ ቤቱ በሁለት ቀናት ቆይታው የአስፈጻሚና የዳኝነት አካሉን የ2010 ዕቅድ አፈጻጸም ገምግሞ አጽድቋል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔት የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ሰሞኑን ባካሄደው ጉባኤ የተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ፣ የከንቲባ ጽህፈት ቤት ኃላፊና የሲቪል ሰርቪስና የሰው ኃብት ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊዎችን መሾሙ ታውቋል፡፡