የሕንድ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት እንዲሰማሩ ድጋፍ ይደረጋል... ሕንድ ኢንቨስተሮች ፎረም - ኢዜአ አማርኛ
የሕንድ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት እንዲሰማሩ ድጋፍ ይደረጋል... ሕንድ ኢንቨስተሮች ፎረም
አዲስ አበባ፤ታህሳስ 13/2013 (ኢዜአ) የሕንድ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ዘርፍ እንዲሰማሩ ድጋፍና ማበረታቻ እንደሚያደርግ የሕንድ ኢንቨስተሮች ፎረም አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በተሻሻለው የኢንቨስትመንት ሕግ ዙሪያ በኢትዮጵያ ለሚገኙ የሕንድ ባለሃብቶች ገለጻ አድርጓል።
በኢትዮጵያ የሕንድ ኢንቨስተሮች ፎረም ሊቀመንበር ማዮር ኮታሪ ለኢዜአ እንዳሉት ፎረሙ የአገራቸውን ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ያሳድጋል።
ኢትዮጵያ ያፀደቀችው አዲሱ የኢንቨስትመንት ዓዋጅ በጉጉት ሲጠበቅ እንደነበረም ተናግረዋል።
ዓዋጁ በተለይም ለውጭ ባለሃብቶች ዝግ የነበሩ ዘርፎችን ክፍት በማድረጉ ባለሀብቶችን ያበረታታል ብለዋል።
የሕንድ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በእርሻ፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በቱሪዝም እንዲሁም በትምህርትና በቴክኖሎጂ ሽግግር መስኮች መስራታቸውንም አስታውሰዋል።
ፎረሙ ከሕንድ የሚመጡ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ኢንቨስትመንት ለማስፋፋት ጥረት እንደሚያደርግም ሊቀመንበሩ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ መኮንን ሀይሉ በአገሪቷ በተካሄደው ሪፎርም በርካታ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለባለሃብቶች ክፍት መደረጋቸውን ይገልጻሉ።
በተጨማሪም በተለያዩ ወቅቶች ጉዳት የደረሰባቸው የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን ወደ ሥራ ለማስገባት ድጋፍ እየተደረገ ነው ብለዋል።
የተሻሻለው የኢንቨስትመንት ዓዋጅ በቀጣይ የውጭ ባለሀብቶችንም ተሳትፎ እንደሚያሳድግ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የሕንድ ባለሀብቶች ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስት ማድረጋቸውን ከአገሪቷ ኤምባሲ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።