የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው እለት ባካሄደው 93ኛው መደበኛ ስብሰባ በሁለት አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ - ኢዜአ አማርኛ
የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው እለት ባካሄደው 93ኛው መደበኛ ስብሰባ በሁለት አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 13/2013 ( ኢዜአ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው እለት ባካሄደው 93ኛው መደበኛ ስብሰባ በሁለት አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።
ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው በካፒታል ገበያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ሲሆን ያደገና የዳበረ የካፒታል ገበያ ለሀገር የኢኮኖሚ ዕድገትና ብልፅግና አስፈላጊ መሆኑን ገልጿል፡፡
የካፒታል ገበያ ባደገበት ሀገር አምራች ኩባንያዎች የአክስዮንና የብድር ሠነዶችን በመሸጥ የረዥም ጊዜ እና የአደጋ ሥጋት ያለባቸውን ነገር ግን የምርታማነት ባህሪ ያላቸውን ፕሮጀክቶች በቀላሉ ፋይናንስ ማድረግ ይችላሉ ብሏል ምክር ቤቱ በመግለጫው።
በሌላ መልኩ ደግሞ የካፒታል ገበያ ለህብረተሰቡ አማራጭ የቁጠባ መንገዶችን በማቅረብ የኢኮኖሚውን የፋይናንስ ቁጠባ ከፍ የሚያደርግ መሆኑ ተመልክቷል።
ይህም ኢንቨስትመንትን በሃገር ውስጥ ቁጠባ ፋይናንስ እንዲሆን በማድረግ ከውጭ ፋይናንስ ያለንን ጥገኝነት ይቀንሰዋል ብሏል፡፡
በዚህ ረገድ የካፒታል ገበያ የሃገሪቱን የክፍያ ሚዛን በማስተካከል ለማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋል፡፡
እነዚህንና ሌሎች የካፒታል ገበያ ጥቅሞችን ታሳቢ በማድረግ ረቂቅ አዋጁ በብሄራዊ ባንክ ተዘጋጅቶ የቀረበ ሲሆን ምክር ቤቱም በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ በዝርዝር ከተወያየ በኋላ አንዳንድ ማስተካከያዎችን በማድረግ ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲመራ መወሰኑን አስታውቋል።
ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ ለማቋቋምና ለማስተዳደር በወጣ ረቂቅ ደንብ ላይም ተወያይቷል፡፡
የፋይናንስ ተቋማት በተለይም የባንኮችና የአነስተኛ ፋይናንስ ተቋማት ሀብት በአብዛኛው የአስቀማጮች ነው፡፡
በመሆኑም የገንዘብ አስቀማጩን ጥቅም ለመጠበቅ መንግሥታት በፋይናንስ ተቋማቱ ላይ ከፍተኛ ቁጥጥርና ክትትል ያደርጋሉ፡፡
ጠንካራ የፋይናንስ ቁመና ያለዉ “ግልፅ” የተቀማጭ ገንዘብ መድን ሥርዓት በተፋጠነ ሁኔታ ብዛት ላላቸው አስቀማጮች ገንዘባቸውን በመመለስ በፋይናንስ ሥርዓቱ ላይ ያለው የሕዝብ አመኔታ እንዲጨምር ያደርጋል ብሏል፡፡
ይህም በተቀማጭ መልክ ከፍተኛ ገንዘብ ወደ ፋይናንስ ዘርፍ እንዲገባ በማድረግ ለኢንቨስትመንትና ለፋይናንስ ሥርዓቱ ጥልቀት ስፋትና አካታችነት እንዲሁም ለኢኮኖሚዉ ዕድገት የበኩሉን አስተዋፅዖ የሚያደርግ መሆኑን በመግለጽ ብሄራዊ ባንክ ረቂቅ ደንቡን አዘጋጅቶ አቅርቧል፡፡
ምክር ቤቱም በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ ሰፊ ውይይት ካደረገ በኋላ በስራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡
ሌላው ምክር ቤቱ የተወያየበት አጀንዳ የመከላከያ ሰራዊት አዋጅ ቁጥር 100/201 ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ የመከላከያ ሰራዊት አደረጃጀት እና አሰራር ዘመኑን በዋጀ እና ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነትን ግምት ውስጥ አስገብቶ በየጊዜው እየተፈተሸ ሊስተካከልና ለውጥ ሊደረግበት የሚገባ ዘርፍ ነው፡፡
ሰራዊቱ እናት አገሩን አሁን ካለው የበለጠ ዘመን ሊያገለግል የሚችልበትን እድል መፍጠር እና አገሪቷም ወጪ አውጥታ፣ ጊዜ ወስዳ ያሰለጠነቻቸውን እና ለአገራዊ ተልዕኮ እና ግዳጅ ብቁ አድርጋ ለተልዕኮ ያሰማራቻቸውን የሰራዊት አባላት ብቁ እና ዘመኑን የሚመጥን አገልግሎት እስከሰጡ ድረስ በሰራዊቱ ውስጥ ሊኖራቸው የሚገባውን የአገልግሎት ዘመን እንደገና መፈተሽና ማስተካከል አስፈላጊ ሆኗል።
በመሆኑም የአገርን ሉዓላዊነት በማስከበር፣ ህገ መንግስቱን እና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ከአደጋ በመጠበቅ፣ የህዝቦችን ዘላቂ ሰላም እና አብሮ የመኖር ዋስትና በማረጋገጥ ረገድ ዋጋ የከፈሉ እና እየከፈሉ የሚገኙ የሰራዊት አባላትን ለአገር የከፈሉትን ውለታ ሊተካ የሚችል ባይሆንም የአገሪቱ አቅም በፈቀደው መጠን ሊያገኟቸው የሚገቡ አገልግሎቶችን፣ ሊደረግላቸው ስለሚገባ ማበረታቻ እና አለም አቀፋዊ ተሞክሮዎችን እና አሰራሮችን እንዲሁም የሰራዊቱን ነባራዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ የሰራዊቱ አባላት እና ኃላፊዎች ልዩ የማዕረግ እድገት እና ሽልማት ሊያገኙ የሚችሉበትን አዳዲስ አሰራሮች በአዋጁ ውስጥ ማካተት በማስፈለጉ ረቂቅ የማሻሻያ አዋጁን ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡
ምክር ቤቱም በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ በዝርዝር ከተወያየ በኋላ አንዳንድ ማስተካከያዎችን በማከል ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲመራ ወስኗል።