ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሃገራት ጋር ያላት ጥብቅ ግንኙነት ተጠናክሮ ይቀጥላል- አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 13/2013 ( ኢዜአ) ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሃገራት ጋር ያላት ጥብቅ ግንኙነትና የትብብር ሂደት ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለጹ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም በቅርቡ በተካሄደው የኢጋድ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በኢትዮጵያ ስለነበረው የህግ ማስከበር ዘመቻ ማስረዳታቸውን ገልጸዋል።

አባል ሃገራቱም ጉዳዩን በአግባቡ መረዳታቸውንና ሂደቱን እንደሚደግፉት አረጋግጠዋል ብለዋል።

አባል ሀገራቱ የሚገጥሟቸውን የጋራ ችግሮች በጋራ ለመፍታት እንዲቻል መግባባት ላይ መድረሳቸውንም አምባሳደር ዲና ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሃገራት ጋር ጥብቅ ግንኙነት እንዳላት ገልጸው በየአጋጣሚው የሚፈጠሩ ጥቃቅን ክፍተቶችን ለእኩይ አላማ ለመጠቀም የሚሹ ሃይሎች አይጠፉም ሲሉ አስረድተዋል።

ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጋር በተገናኘ የተለየ ፍላጎት ያላቸው መኖራቸውንም ጠቅሰዋል።

ሰሞኑን በሱዳንና በኢትዮጵያ ድንበር አካባቢ የሚታየውን ጊዜያዊ ችግር ለአብነት የጠቀሱት አምባሳደር ዲና ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በመሪዎች ደረጃ መልካም ፈቃድ መኖሩን ገልጸዋል።

በሱዳን በመጠለያ የሚገኙ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ከሱዳን መንግስት ጋር ወደ ስምምነት እየተደረሰ ነው ብለዋል።

ይሁን እንጂ የዜጎችን ስደት የኢኮኖሚና ፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚጥሩ አካላት በሱዳን ቋሚ ስደተኛ እንዲኖር የማድረግ ፍላጎት አላቸው ብለዋል።

አምባሳደር ዲና በመግለጫቸው ባሳለፍነው ሳምንት ኢትዮጵያ ከተለያዩ ሃገራት ጋር የትብብር ግንኙነቶችን የሚያጠናክሩ ስራዎችን ማከናወኗን ገልጸዋል።

የህዝብ ለህዝብ ዲፕሎማሲን ለማጠናከር ሲባል አረብኛና ፈረንሳይኛን ጨምሮ በተለያዩ ቋንቋዎች ከሚጽፉ የማህበራዊ አንቂ ወይም አክቲቪስቶች ጋር ውይይት መካሄዱንም አስታውሰዋል።

ባለፈው ሳምንት 327 ዜጎች ከሳውዲ አረቢያ ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ ተደርጓልም ብለዋል።

የአውሮፓ ህብረት ለኢትዮጵያ ከሚደግፈው ገንዘብ ውስጥ 90 ሚሊዮን ዩሮ ሰረዘ ተብሎ የተናፈሰው ወሬም ሃሰት መሆኑን ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ህብረት ቃል የተገባላትን ድጋፍ ከ90 በመቶ በላይ መጠቀሟንና  ቀሪው በሂደት ላይ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም