ቀጥታ፡

የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ወረርሽኙን የመከላከል ሃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 13/2013 ( ኢዜአ) ጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን በመከላከል ረገድ የተጣለባቸውን ሃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ ጥሪ አቀረበ።

ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እስካሁን የተደረገው ጥረት መና እንዳይቀር የጥንቃቄ እርምጃው ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ተብሏል።

ጤና ሚኒስቴር በዓለም አቀፍና በኢትዮጵያ ስርጭቱ እየተስፋፋ የመጣውን የኮሮና ቫይረስ አስመልክቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል።

በኢትዮጵያ ቫይረሱ መከሰቱን ተከትሎ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ መንግስትና የሚመለከታቸው አካላት ከፍተኛ የጥንቃቄ እርምጃዎችን ሲወስዱ መቆየታቸውም ተገልጿል።

ይሁንና ወረርሽኙ የተፈራውን ያህል የከፋ ችግር ባያስከትልም በሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ዘንድ እየታየ ያለው መዘናጋት ዋጋ ያስከፍላል የሚል ስጋት ፈጥሯል።

የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አስቻለው አባይነህ ቫይረሱ ኢትዮጵያ ከመግባቱ በፊትና በኋላ እየተወሰዱ ስላሉ የጥንቃቄ እርምጃዎች አብራርተዋል።

በአገሪቷ አሁን እየተደረገ ባለው ምርመራ በየቀኑ በአማካይ 400 ሰዎች ቫይረሱ እንደሚገኝባቸው ገልጸው ይህም ካለው የምርመራ አቅም አኳያ እንጂ ቁጥሩ ሊያሻቅብ እንደሚችል አልሸሸጉም።

ወረርሽኙ በዓለምም ሆነ በኢትዮጵያ በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ ቢሆንም ቀደም ሲል ይደረጉ የነበሩ የጥንቃቄ እርምጃዎች ግን እየተዘነጉ መጥተዋል ነው ያሉት።

አዲስ አበባን ጨምሮ  በተለያዩ ክልሎች የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል የሚጠቀሙ ሰዎች ቁጥር መቀነሱንም ገልጸዋል።

በመገናኛ ብዙሃን ሞዴል ሊሆኑ የሚችሉ ግለሰቦች የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ሳያደርጉና ሲጨባበጡ መታየታቸው 'አስደንጋጭና አሳሳቢ ነው' ብለዋል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው በአገር አቀፍ ደረጃ ለኮሮና ቫይረስ እየተሰጠ ያለው ትኩረት መቀነሱን ነው የተናገሩት።

ትምህርትና ሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎቶች መጀመራቸውን ተከትሎ የጥንቃቄ እርምጃው መጠናከር ሲገባው መዘናጋቱ ወረርሽኙ የከፋ ጉዳት እንዲያደርስ ያደርጋል ብለዋል።

በተለይም ወረርሽኙን ለመከላከል የወጡ መመሪያዎች በመንግስት የስራ ሃላፊዎች ጭምር መጣሳቸው መዘናጋቱ እንዲባባስ አድርጓል ነው ያሉት ዶክተር ሊያ።

"ወረርሽኙን እየተከላከልን የተጣለብንን የስራ ሃላፊነት በአግባቡ ልንወጣ ይገባል" ያሉት ሚኒስትሯ የእስከዛሬው ኮቪድን የመከላከል ልፋት ከንቱ እንዳይቀር የጥንቃቄ እርምጃው ይጠናከር ሲሉ አሳስበዋል።

በዓለም ላይ 77 ሚሊዮን ሰዎች በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሲሆን 1 ነጥብ 7 ሚሊዮኑ ደግሞ በዚሁ ሳቢያ ሕይወታቸውን አጥተዋል።

በኢትዮጵያም ከ120 ሺህ በላይ ዜጎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል፤ እስከ ትናንትና ድረስም 1 ሺህ 861 ሰዎች በኮሮናቫይረስ ምክንያት ለሕልፈት ተዳርገዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም