ጁንታው ቢወገድም የቀሩት ርዝራዦቹ ስጋት እንዳይፈጥሩ መታገል እንደሚገባ ተመለከተ - ኢዜአ አማርኛ
ጁንታው ቢወገድም የቀሩት ርዝራዦቹ ስጋት እንዳይፈጥሩ መታገል እንደሚገባ ተመለከተ

ሀዋሳ ታህሳስ 13ቀን 2013( ኢዜአ) ጁንታው ህወሀት ህግ በማስከበሩ ዘመቻ ቢወገድም የቀሩት የጥፋት ርዝራዦቹ ስጋት እንዳይፈጥሩ መታገል እንደሚገባ ተመለከተ።
የሲዳማ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይና በአምስት ወራት የሥራ አፈፃፀሙ ዙሪያ ከወረዳና ከተማ አስተዳደር አመራሮቹ ጋር ተወያይቷል፡፡
የሊጉ ፕሬዝዳንት ወይዘሮ እመቤት ኢሳያስ በውይይቱ ወቅት ጁንታው ህወሃት የሀገሪቱን ሥልጣን በበላይነት ተቆጣጥሮ በቆየባቸው 27 ዓመታት በሚፈጠራቸው የፖለቲካ ሴራ እርስ በእርስ ሲያጋድለን ኖሯል ብለዋል፡፡
ቡድኑ መንግስት በወሰደው ሕግን የማስከበር ዘመቻ ቢወገድም በየአካባቢው የቀሩት የጥፋት ርዝራዦቹ ስጋት እንዳይፈጥሩ መታገል እንደሚገባ አመልክተዋል።
ሴቶች በማህበራዊ መስተጋብራቸው በአካባቢያቸው የሚስተዋል ማንኛውንም እንግዳ ጉዳይ ቀደመው የማወቅ አጋጣሚ እንዳላቸው ገልፀው በተላላኪዎቹ ስጋት እንዳይፈጥር መከላከል እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።
የሴቶች ሊግ አመራሮች አደረጃጀቶችን በመጠቀም ሴቶችን በአመለካከት ማብቃትና ጁንታው የዘረጋው የጥፋት መረብ ተበጣጥሶ እስኪያልቅ ድረስ የመታገል ሚናቸውን መወጣት እንደሚኖርባቸውም አሳስበዋል፡፡
የመልጋ ወረዳ ሴቶች ሊግ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሪት እመቤት ማቴዎስ በሰጠችው አስተያየት በየአካባቢው ያሉ የጁንታው ርዝራዦች በአካልም ሆነ በማህበራዊ ትስስር አማካይነት ትርምስ ለመፍጠር ጥረት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከወረዳ እስከ ቀበሌ ያሉትን የሴቶች አደረጃጀቶች በማቀናጀት በህዝቡ ውስጥ ያሉ የጥፋት ተላላኪዎችን የመለየት ሥራ እየሰራን ነው ብለዋል፡፡
አሁን ላይ አካባቢያችን የተረጋጋ ቢሆንም ሁሌም ቢሆን ሠላማችንን ነቅተን መጠበቅ ይገባናል ያሉት ደግሞ የቡርሳ ወረዳ ሴቶች ሊግ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ታሙኔ ታደሰ ናቸው።
ሴቶች በማህበረሰቡ ውስጥ ባላቸውን ዘርፈ ብዙ ተሳትፎ የአካባቢቸው ሠላም ተጠብቆ እንዲቆይ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ግንዛቤ ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል ፡፡
በውይይት መድረኩ የክልሉ እንዲሁም የወረዳና ከተማ አስተዳደሮች የሴቶች ሊግ አመራሮች ተሳትፈዋል።