ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ያዘጋጀው ሻምፒዮና በአዲስ አበባ መካሄድ ጀመረ

አዲስ አበባ ታህሳስ 132013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ያዘጋጀው የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲዬም ተጀመሯል። 

ሻምፒዮናው የአጭር፣ የመካከለኛ፣ የሶስት ሺህ ሜትር መሰናክል፣ የእርምጃና የሜዳ ተግባራትን ያካተተ ነው።

በኢትዮጵያ ኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በተዘጋጀው በዚህ ሻምፒዎና ከ27 ክለቦችና ተቋማት የተውጣጡ 713 አትሌቶች ይካፈላሉ።

ውድድሩም እስከ ታህሳስ 18 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ ይሆናል።

ሻምፒዮና ሲጀመር በሴቶች የአሎሎ ውርወራና በወንዶች የስሉስ ዝላይ የፍጻሜ ውድድሮች ተደርገዋል።

እንዲሁም በሁለቱም ፆታዎች የ800 ሜትር፣የ400 ሜትር መሰናክልና የ100 ሜትር ርቀት ሩጫ ማጣሪያ ውድደሮች ተካሂደዋል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የውድድርና ተሳትፎ የሥራ ሂደት መሪ አቶ አስፋው ዳኜ ሻምፒዮናው የኮቪድ -19 መከላከያ ፕሮቶኮል በጠበቀ መልኩ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

በሻምፒዮናው በርካታ አዳዲስ አትሌቶች እንደሚሳተፉበትም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በየዓመቱ የሩጫ፣የውርወራና የዝላይ ውድድሮች የሚያካሂድበት ሻምፒዮና እንደሚያካሄድ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም